የጉራጌ ህዝብ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ን የአመራር ሂደት በተግባር በመደገፍ የለውጡን ስኬቶች ለማስቀጠል በቁርጠኝነት ይሰራል 

97

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፦ የጉራጌ ህዝብ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ን የአመራር ሂደት በተግባር በመደገፍ የለውጡን ስኬቶች ለማስቀጠል በቁርጠኝነት እንደሚሰራ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ  ክልል  ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።

የለውጡን መንግስት የሚደግፍ ሕዝባዊ መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በወልቂጤ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።


 

በሕዝባዊ መድረኩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ን ጨምሮ የፌደራል፣ የክልልና የዞን አመራሮች እንዲሁም የከተማው ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆን ለውጡን የሚደግፉ የተለያዩ መልዕክቶችን  አስተላልፈዋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል  ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በስነስርዓቱ ባስተላለፉት መልዕክት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመሻገርና በመደመር ተምሳሌትነት የጉራጌን ህዝብ አክብረው ስለመጡ ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል።

የትጋትና የአብሮነት ምሳሌ ወደ ሆነው የጉራጌ ማህበረሰብ እንኳን ደህና መጣችሁ ያሉት ምክትል ርዕሰ መሰተዳድሩ የጉራጌ ህዝብ ከወንድሞቹ ኢትዮጵያውያን ጋር ለሀገራዊ ለውጡ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ለውጡን እውን በማድረጉ ሂደት የጉራጌ ህዝብ ሚና ከፍተኛ እንደነበር አቶ እንዳሻው ጣሰው አመልክተዋል።

አክለውም የለውጡ መንግስት ያመቻቸውን የለውጥ ሂደት በመጠቀም እና በመደመር እሴት መዛነፎችን በሰከነ ሂደት በማረም በጋራ የማደግን አደረጃጀት ተግባራዊ አድርጓል ብለዋል።

በዚህም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እንዲሁም ሌሎች መስኮች ያለውን ከፍተኛ ሚና አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

የጉራጌ ህዝብ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ን የአመራር ሂደት በተግባር በመደገፍ የለውጡን ስኬቶች ለማስቀጠል በቁርጠኝነት ይሰራል ሲሉ አስታውቀዋል።

የለውጡን ሂደት በሁሉም መስኮች ለማፋጠን የጉራጌ እና የክልሉ ህዝብ ቃሉን ያድሳል ለውጡን ይደግፋል ሲሉም ተናግረዋል።

የክልሉ ህዝብም ያለውን እምቅ አቅም ወደ እሴት በመቀየር የለውጡን ሂደት በተጨባጭ ውጤቶች እያረጋገጠ ድጋፉን እንዲያጠናክር መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም