በዞኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ማስፋፋት ላይ ትኩረት ተደርጓል

94

ሚዛን አማን ፤ ሚያዝያ 12/2016 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቤንች ሸኮ ዞን የስፖርት ባህልን ይበልጥ ለማዳበር የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ማስፋፋት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን  የዞኑ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ጌታቸው ኮይካ ለኢዜአ እንደገለጹት ስፖርተኞችን ለማፍራት የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራዎችን ማስፋፋት ላይ ትኩረት የተደረገ ሲሆን የውድድር ሜዳዎችን ማመቻቸት ቀዳሚ ተግባር ነው።

ለዚህም ዞኑ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው የተለያዩ ሀገር አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮችን ሊያስተናግድ የሚችል የሚዛን አማን ሁለገብ ስታዲየም ከ82 ሚሊዮን በሚበልጥ ወጪ እየተገነባ መሆኑን ተናግረዋል።

ስታዲዮሙ የመልበሻ ክፍል፣ የአስተዳደር እና የቴክኒክ ቢሮዎች ያሉት እና አነስተኛ አዳራሽ እንዲሁም መለስተኛ ካፍቴሪያን የያዘ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

አፈጻጸሙ 62 በመቶ ላይ ደርሶ በከፊል አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸው የተለያዩ ጨዋታዎችን ለመመልከት የሚያስችል ደረጃ አንድ ወይም ቪ አይ ፒ መቀመጫዎች እንደሚገጠሙለት ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ከሚዛን አማን ሁለገብ ስታዲየም ከፍ ያለ ሁለተኛ የስታዲየም ግንባታ በሲዝ ከተማ አስተዳደር ለማስጀመር ሂደቱ እየተጠናቀቀ ይገኛል ብለዋል።

በሌላ በኩል በትምህርት ቤቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በማስፋፋት ለተማሪዎችና ለአካባቢው ነዋሪዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ በተደረገው ጥረት ባለፉት 9 ወራት ውስጥ 65 የስፖርት ሜዳዎችን ማመቻቸት ተችሏል ብለዋል።

በወረዳ ደረጃ 18 የይዞታ ማረጋገጫ የተሰጣቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች መኖራቸውን ገልጸው በአግባቡ ተንከባክቦ የመጠበቅ እና የመጠቀም ኃላፊነትን ወጣቶችና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዲወጡም አሳስበዋል።

የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪው አቶ ዐቢዩ ዳኜ፤ አዕምሯችን እረፍት እንዲያገኝና ልጆቻችን በስፖርት ተኮትኩተው እንዲያደጉ ለማስቻል የስፖርት ማዘወተሪያ ሜዳ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

እየተገነባ ባለው የሚዛን አማን ሁለገብ ስታዲየም ከሥራ መልስ ገብተው እረፍት እንደሚያደርጉ እና ጠዋት ጠዋት የጤና ስፖርት እንደሚሠሩበትም ተናግረዋል።

ወጣቶች አላስፈላጊ ቦታ ላይ እንዳይውሉ ከማድረግ ባሻገር ነገ ሀገር ማስጠራት የሚችሉበትን ስፖርታዊ ዝግጅት እንዲያደርጉ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ መኖር ወሳኝ በመሆኑ የሚጠበቅብንን እንደግፋለን ብለዋል።

በስፖርት ማዘውተሪያ የኳስ ልምምድ ሲያደርጉ ካገኘናቸው መካከል ሚካኤል ደረጀ እንዳለው ስፖርት ጤንነትን ለመጠበቅ እና አብሮነትን ለመፍጠር ይጠቅማል።

ነገ የተሻለ እግር ኳስ ተጫዋች በመሆን ትላልቅ ውድድሮች ላይ የመሳተፍ ራዕይ ይዞ ጠዋትና ማታ በሚዛን ሁለገብ ስታዲየም ከጓደኞቹ ጋር ልምምድ እንደሚያደርግ ተናግሯል።

ስታዲየሙ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መገንባቱ ውድድሮች ሲደረጉበት ልምድ የመቅሰም እድልን ይዞ ይመጣል ያለው ደግሞ ታዳጊ እውነቱ ብርሃኑ ነው።

ከትምህርት ውጪ ያለውን ጊዜ የምናሳልፍበት በመሆኑ የሜዳውን እና በውስጡ የሚኖሩ ንብረቶችን የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነታችንን እንወጣለን ብሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም