የቱሪዝም ሀብትን ከማስተዋወቅ ጎን ለጎን የቱሪስት ቆይታን የሚያራዝሙ የመዳረሻ ልማት ስራዎችን በትኩረት እያከናወኑ መሆኑን የተለያዩ ክልሎች ገለጹ

60

አዲስ አበባ፣ ሀዋሳ፣ ሐረር፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፦ በየአካባቢያቸው ያለውን የቱሪዝም ሀብትን ከማስተዋወቅ ጎን ለጎን የቱሪስት ቆይታን የሚያራዝሙ የመዳረሻ ልማት ስራዎችን በትኩረት እያከናወኑ መሆኑን የተለያዩ ክልሎች ገለጹ።

መንግስት የቱሪዝም ዘርፉን እንደ ትልቅ የኢኮኖሚ ዘርፍ ወስዶት ዘርፉን የሚያነቃቁ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አማካኝነት 'ገበታ ለሸገር'፤ 'ገበታ ለአገር'ና አሁን ደግሞ 'ገበታ ለትውልድ' በሚሉ መርሃ ግብሮች የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ስራዎች በመካሄድ ላይ ናቸው።

በዚሁ ጉዳይ ኢዜአ ከኦሮሚያ፣ ከሐረሪና ከሲዳማ ክልሎች የዘርፉ ኃላፊዎች ጋር ቆይታ ያደረገ ሲሆን፣ ክልሎቹም ያላቸውን የቱሪዝም ሀብት ከማስተዋወቅ ጎን ለጎን የጎብኚዎችን ፍላጎት የሚያሟሉ የመዳረሻ ልማት ስራዎች እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ክልሉ በርካታ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን የታደለ ቢሆንም፤ ቀድሞ ለዘርፉ በተሰጠው አነስተኛ ትኩረት የመዳረሻ ልማት ላይ ውጤታማ ስራ እንዳልተሰራ ገልጿል።

በቢሮው የቱሪዝም ልማትና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ ፋንታሁን ታደሰ  እንደሚሉት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የቱሪስት መስህብ ስፍራ መዳረሻዎችን ማልማት ተጀምሯል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በማዕከላዊ ኦሮሚያ አካባቢ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች የመንገድና ማረፊያ ቦታዎችን ከማሟላት አኳያ የተሻለ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም በምስራቅ ኦሮሚያና በደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ አካባቢዎች የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ለማልማት የተጀመሩ ጥረቶች ይጠናከራሉ ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ጎብኚዎች አንድ የመስህብ ስፍራ ብቻ ተመልክተው እንዳይመለሱ ለማድረግ በቅብብሎሽ መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ ትኩረት መደረጉን አቶ ፋንታሁን አስታውቀዋል።

በክልሉ በስፋት ከሚጎበኙ ስፍራዎች መካከል የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በኢትዮጵያ ሁለተኛው ታላቅ የተፈጥሮ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው ይገኝበታል።

ወደ ባሌ አካባቢ የሚያቀና ጎብኚ የባሌ ታራሮች ብሔራዊ ፓርክን፣ ሀረና ቡሉቅ ጥቅጥቅ ደን፣ ድሬ ሼክ ሁሴንና ሶፍ ኡመር ዋሻን ጎብኝቶ እንዲመለስ የመስህብ ስፍራዎችን በመንገድ የማስተሳሰር ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

 የጎብኚዎች የቆይታ ጊዜ የበለጠ እንዲራዘም የማረፊያ ልማት ስራም ከግል ዘርፉ ጋር በትብብር እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው በዚህ ሂደት የመስህብ ስፍራዎቹ ከሚገኙባቸው የአካባቢ መስተዳደሮች ጋር በቅንጅትና በትብብር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።


 

በሐረሪ ክልልም የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ባህል፣ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ አስታውቋል።

የቢሮው ሐላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ እንዳስታወቁት ክልሉ በርካታ ጥንታዊ፣ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ የመስህብ ስፍራዎች ያሉት ሲሆን የመስህብ ስፍራዎቹ በአገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ይዘወተራሉ።

የመስህብ ስፍራዎቹን ለጎብኚዎች ምቹና ሳቢ ለማድረግ በተለየ ትኩረት መሰራቱን ተናግረው ቀደም ሲል ከጽዳትና ከሌሎች ችግሮች ጋር በተያያዘ በክልሉ የጎብኚዎች ቆይታ እምብዛም አልነበረም ሲሉ ይገልጻሉ።

በአሁኑ ወቅት ግን ክልሉን ለነዋሪው ምቹ፣ ለጎብኚው ሳቢ የማድረግ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ ጎብኚዎችን ከሚስቡ የመስህብ ስፍራዎች መካከል የ'ጀጎል ግንብ' አንዱ ሲሆን የሐረር ጀጎል ግንብ የተገነባው በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአህመድ ግራኝ ጦርነት በኋላ በአሚር ኑር አማካኝነት የሐረርን ከተማ ከወራሪዎች ለመከላከል ሲባል የተገነባ ነው።

በተሰራው ስራም የጀጎል ግንብን ጨምሮ በሐረር የሚገኙ ሙዚየሞች እንዲሁም በርካታ ጥንታዊ፣ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ የመስህብ ስፍራዎችን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር መጨመሩን ነው የገለጹት።

በክልሉ የ'ኢኮ ፓርክ' ግንባታ እየተፋጠነ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን በክልሉ ገጠር ቀበሌ የሚገኙ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችንና ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ ጎብኚው የሚያሳልፍባቸው ስፍራዎችና የቱሪስት ቁሳቁሶች የሚሸጡባቸው ቦታዎችን የማበልጸግና ቅርሱን በጠበቀ መልኩ የመስራት ሂደቶች ጥናት ላይ መሆኑንና በቀጣይ ዓመታት ተግባራዊ እንደሚሆኑም አስረድተዋል።


 

የሲዳማ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አቶ አበበ ማሪ፣ በክልሉ ለመዳረሻ ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የቱሪስቱን የቆይታ ጊዜ ማራዘም የሚያስችሉ የመሰረተ ልማት ዝርጋቶችና የመሰተንግዶ ስራን ለማዘመን ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በሲዳማ ክልል በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡት መካከል አንዱ የሲዳማ ዘመን መለወጫ 'ፊቼ ጨምበላላ' በዓል ሲሆን ይህም በርካታ ጎብኚዎችን የሚያስተናግድ ሁነት ነው።

በቀጣይም ያሉትን መልካም እድሎች በአግባቡ በማልማትና በማስተዋወቅ በክልሉ የቱሪስት ፍሰትን በእጥፍ ለመጨመር መታቀዱን ገልጸዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም