የፕላስቲክ ውጤቶች አጠቃቀምና አወጋገድን በማዘመን የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቷል--ባለስልጣኑ

172

አርባ ምንጭ ፤ ሚያዝያ 12/2016 (ኢዜአ)፦ የፕላስቲክ ውጤቶች አጠቃቀምና አወጋገድ ስርአትን በማዘመን የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል ትኩረት መሰጠቱን የኢፌዴሪ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

“ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ” በሚል መሪ ሃሳብ ክልል አቀፍ የብክለት መከላከል ንቅናቄ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።


 

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬነሽ መኩሪያ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የፕላስቲክ ውጤቶች አጠቃቀምና አወጋገድ ስርአትን በማዘመን ሀገርን ከአካባቢ ብክለት የጸዳች ለማድረግ በትኩረት ይሰራል።

የፕላስቲክ ቆሻሻዎች በመሬት ውስጥ ለዘመናት ሳይበሰብሱ በመቆየት ስነ-ምህዳርን በማዛባት፣ ምርትና ምርታማነት በመቀነስ እንዲሁም የውሃ አካላትን በመበከል በሰውና በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተሉ ይገኛሉ ብለዋል።

የፕላስቲክ ውጤቶች አካባቢን የመበከል፣ የማቆሸሽና መሠረተ ልማቶችን ከመጉዳት ባለፈ ለማህበረሰቡ የጤና ጠንቅ የሚሆኑበት ሁኔታ መኖሩንም ነው ያስረዱት።

የፕላስቲክ ውጤቶች አጠቃቀምና አወጋገድ ሥርአት ላይ የባህሪ ለውጥ ባለመምጣቱ በሰው ልጆች ላይም  ጉዳት እያደረሰ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም የፕላስቲክ ውጤቶችን በአግባቡ የመጠቀምና የማስወገድ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ ወይዘሮ ፍሬነሽ ተናግረዋል።

በአካባቢ ደህንነት መብት አዋጅ አንቀጽ 44 መሠረት ሁሉም ሰው ንጹህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት እንዳለው ጠቅሰው፣ የፕላስቲክ ውጤቶችን አወጋገድ በማዘመን የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

ዳይሬክተሯ እንዳሉት እንደ ሀገር የቆሻሻ አወጋገድ ስርአትን ለማዘመንና ቆሻሻን በመልሶ ዑደት ጥቅም ላይ ለማዋል በከተሞች የተጀመሩ ሥራዎችን ለማጠናከር ይሰራል።

በእዚህ ረገድ የተጀመሩ ሥራዎችን በሁሉም የሀገሪቱ ከተሞች ለማስፋትና ለሥራ ዕድል መፍጠሪያነት ለማዋል ባለስልጣኑ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

የፕላስቲክ ምርቶች ከሚሰጡት ጥቅም ይልቅ የሚያስከትሉት ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡ በፕላስቲክ ምትክ ባህላዊ ቁሶችን መጠቀም እንዳለበት አስገንዝበዋል።

እንደሀገር ቆሻሻ አወጋገድ ሥርአቱን ለማዘንም ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።  

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ግዛቴ ግጄ በበኩላቸው እንዳሉት የፕላስቲክ ቁሶች በሰው፣ በእንስሳትና በዕጽዋት ላይ ጉዳት እያስከተሉ ነው።


 

"የፕላስቲክ አጠቃቀማችን ኋላ ቀር በመሆኑ ፕላስቲኮችን በቸልተኝነት በየስፍራው እንጥላለን" ያሉት አቶ ግዛቴ፣ በዘፈቀደ የሚጣሉ ፕላስቲኮች በአካባቢ ስነ-ውበት ላይም አሉታዊ ጫና እየፈጠሩ ነው ብለዋል።

የፕላስቲክ ውጤቶች አገልግሎት ከሰጡ በኋላ ለመልሶ ዑደት ካልዋሉ በነፋስና ጎርፍ ተወስደው ከተሞችን፣ የእርሻ ማሳዎችና የውሃ አካላትን ከመጉዳት ባለፈ የሰው ልጅ፣ የዱርና የቤት እንስሳትን የምግብ ሰንሰለት ያውካሉ ብለዋል።

በአርባ ምንጭ ከተማ የሚጣሉ የፕላስቲክ ቆሻሻዎች በጎርፍ ተወስደው በአባያና ጫሞ ሐይቆች መካከል ከ70 ሄክታር በላይ የደን ሀብትን ከጥቅም ውጭ ማድረጋቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

እንደ ክልል ፕላስቲክ ቆሻሻን በመልሶ ዑደት ጥቅም ላይ ለማዋል፣ ፕላስቲኮችን መልሶ ለሌላ አገልግሎት ለመጠቀምና በምትኩ በቀላሉ ሊበሰብሱ የሚችሉ ምርቶችን ለመጠቀም ህዝባዊ ንቅናቄ መጀመሩንም ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ አካባቢውን ከብክለት በመጠበቅ የተጀመረው ንቅናቄ ከግብ እንዲደርስ ጠንካራ ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባም አቶ ግዛቴ አሳስበዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ “ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ” በሚል መሪ ቃል ሀገር አቀፍ የአካባቢ ብክለት መከላከል ንቅናቄን ባለፈው መጋቢት ወር ማስጀመራቸው የሚታወስ ነው።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም