የኮሪደር ልማት ሰራው የመዲናዋን አረንጓዴ ሽፋን ለማሳደግ ሚናው የጎላ ነው - የአዲስ አበባ ከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ

85

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2016 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ የመዲናዋ አረንጓዴ ሽፋን ለማሳደግ ሚናው የጎላ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ቁጥር እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የመሰረተ ልማት ፍላጎቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጥተዋል፡፡

ይህንንም ለዓመታት የተሻገሩ የመሰረተ ልማት ችግሮች ለመፍታት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ የኮሪደር ልማት ስራ ተጠቃሽ ነው፡፡

የኮሪደር ልማት ስራው ሲጠናቀቀም የህብረተሰቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ከመመለስ ባለፈ የመዲናዋን ውበትና ገጽታ የሚቀይር ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ይመኙሻል ታደሰ፤ ከዚህ ቀደም የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ከአረንጓዴ ልማት ጋር የተሳሰሩ እንዳልነበሩ ተናግረዋል፡፡ 

ይህም ከተማዋን የሚመጥናት ገጽታን እንዳትላበስ አድርጓት መቆየቱን ነው ያነሱት፡፡

ካለፉት 5 ዓመታት ወዲህ የከተማዋን እድገት ከአረንጓዴ ልማት ጋር በማስተሳሰር ውብ ጽዱና ለዜጎቿ የምትመች ከተማ መፍጠር ላይ የተሻለ ስራ መከናወኑንም ጠቁመዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ ደግሞ የከተማዋን ውበትና አረንጓዴ ሽፋን ለመጨመር ለሚከናወኑ ስራዎች ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

የኮሪደር ልማት ስራው በተለይ በከተማዋ መስፈርትን በጠበቀ መልኩ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሮችን ለማከናወን ማነቆ የሆኑ ችግሮችን እንዲፈቱ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ነው የገለጹት፡፡

ይህም የከተማዋን የቱሪስት ፍሰትና የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ያግዛል ነው ያሉት፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት የተከናወኑ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች የከተማዋን የአረንጓዴ ሽፋን ከነበረበት 2 ነጥብ 8 ወደ 15 በመቶ እንዲያድግ ማድረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም