በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ለሌሎች ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በምሳሌነት የሚወሰዱ ናቸው - የኮሙኒኬሽን አመራሮችና ባለሙያዎች

64

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2016 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ለሌሎች ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በምሳሌነት የሚወሰዱ መሆናቸውን የተለያዩ የኮሙኒኬሽን አመራሮችና ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡

ከተለያዩ የፌደራል መስሪያ ቤቶች፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የኮሙኒኬሽን አመራሮችና ባለሙያዎች በመዲናዋ የተከናወኑ እና በሂደት ላይ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።


 

ወዳጅነትና አንድነት ፓርክ፣ የታችኛው ቤተ መንግስት፣ ዓድዋ መታሰቢያ፣ አብርሆት ቤተ መጽሃፍት እና የጫካ ፕሮጀክት ጉብኝት የተደረገባቸው ስፍራዎች ናቸው።

የሐዋሳ ከተማ ኮሙኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ ምርጫዬ ደመቀ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በመዲናዋ የተከናወኑ ልማቶች በትጋት ከተሰራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀገራዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚቻል ትልቅ ማሳያ ናቸው።

በአገር አቀፍ ደረጃ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ማጠናቀቅን የሚያስተምሩ እና የአመራሩን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።


 

የስልጤ ዞን ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ሳሊ ሐሰን በበኩላቸው፤ በየአካባቢው የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በቁርጠኝነት ለመፈፀም ከመዲናዋ የልማት ስራዎች ትልቅ ተሞክሮ ወስደናል ብለዋል።

በተለይም በስልጤ ዞን በመገንባት ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ማጠናቀቅ እንደሚቻል ተምረናል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ከለውጡ በኋላ የተካሔዱ የልማት ስራዎች ስኬታማ እና የሚያስደንቁ መሆናቸውን የተናገሩት የኮንታ ዞን የኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አበበ ጎበና ናቸው።

በዞኑ የተገነቡት የኮይሻ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ፣ በአፍሪካ ትልቁ የዝሆን ዳና ሎጅ፣ የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክና ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች ከለውጡ ወዲህ የተካሔዱ ስኬታማ ስራዎች መሆናቸውን በማሳያነት ገልጸዋል።

የሐረሪ ክልል የኮሙኒኬሽን ሚዲያና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጀዲዳ አህመድ በበኩላቸው በአዲስ አበባ የተገነባው የዓድዋ መታሰቢያ ትውልዱ የጋራ እውነተኛ ታሪኩን በትክክል የሚረዳበት መሆኑን ተናግረዋል።

በዋናነትም የአሁኑ ትውልድ የጥንት አባቶቹ ከፈፀሙት ጀግንነት ተነስቶ ለሀገሩ እድገት የበኩሉን መወጣት እንዳለበት የሚያስተምር ነው ብለዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም