መሰረታዊና የህዝብ ተሳትፎ ያማከለውን የመጀመሪያ ምዕራፍ ሥራ በአጥጋቢ ሁኔታ አገባድጃለሁ- ኮሚሽኑ 

286

ሀዋሳ ፤ ሚያዚያ 11/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መሰረታዊና የህዝብ ተሳትፎ ያማከለውን የመጀመሪያ ምዕራፍ ሥራ በአጥጋቢ ሁኔታ ማገባደዱን ገለጸ።

በኦሮሚያ ክልል በዞን፣ በወረዳና በከተማ አስተዳደር ደረጃ በምክክር ሂደቱ የሚሳተፉ የህብረተሰብ ተወካዮች ልየታ የማጠቃለያ መድረክ ዛሬ በሻሸመኔ ከተማ ተካሄዷል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኮሚሽኑ መሰረታዊና የህዝብ ተሳትፎ ያማከለውን የመጀመሪያ ምዕራፍ ሥራ በአጥጋቢ ሁኔታ አገባዷል። 

በአገሪቱ በአሥር ክልሎች፣ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊዎች ልየታና መረጣ ሥራ 95 በመቶ መከናወኑን ገልፀዋል።


 

በአንዳንድ የሶማሌ ክልልና የድሬዳዋ አስተዳደር ወረዳዎች ያልተጠናቀቀውን የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች ልየታና መረጣ ተግባር በቀጣዩ ሳምንት ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህ አፈፃፀም ስኬታማነት የሲቪል ማህበረሰቡ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መምህራን፣ እድሮች፣ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳ መስተዳድርና ፍትህ አካላት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

የተሳታፊዎች ልየታና መረጣ በተጠናቀቀባቸው ክልሎችና ከተሞች ውስጥ አጀንዳ መሰብሰብ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

''በቀጣይ ሀገራዊ ችግሮቻችንን ሁሉ በአጀንዳ መልክ በማምጣት ተወያይተንና ተመካክረን መግባባት ላይ መድረስ ይጠበቅብናል'' ብለዋል።

በአማራ ክልልም የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች ልየታና መረጣ ለማካሄድ ኮሚሽኑ ከ10 ዩኒቨርሲቲዎች 26 ምሁራንን በመምረጥ ተባባሪ አካላትን እያዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በተመሳሳይም በትግራይ ክልል የምክክር ሂደቱን ለማሳለጥ ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን ብለዋል።

የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ሒሩት ገብረስላሴ በበኩላቸው፤ በምክክሩ ላይ ለመሳተፍ የተመረጡ አካላት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል።

በተለይ ከመጡበት ማህበረሰብ ወሳኝ አጀንዳ በማምጣት በቀጣይ በሚካሄደው ምክክር ላይ በሚገባ ለማስረዳት ከወዲሁ እንዲዘጋጁም  አስገንዝበዋል።

''በዓለም ላይ በጦርነት የተፈታ ችግር የለም'' ያሉት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፤ ይህንን በመረዳት ስለምክክሩ አስፈላጊነት በየአካባቢያቸው ላለው ማህበረሰብ በመግለጽ ማስረዳት እንደሚኖርባቸውም አብራርተዋል።

በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ቦረና ዞን የነገሌ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ከዋጭሌ፣ ዳሳ፣ አሬሮ፣ መደወላቡ፣ ጉሮዶላና ሊበን ወረዳዎች የተውጣጡ 500 የሚጠጉ የኅብረተሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም