በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተወዳዳሪና የሰለጠነ የሰው ሃይል እንዲኖር የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል- የስራና ክህሎት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተወዳዳሪና የሰለጠነ የሰው ሃይል እንዲኖር የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል- የስራና ክህሎት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 11/2016 (ኢዜአ)፦ በአገሪቱ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ብቃት ያለውና ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ሃይል ለማፍራት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ገለፁ።
የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ''የተቋማዊ የለውጥ ስራዎችን በማፅናት የላቀ ምርታማነትን እናረጋግጣለን'' በሚል መሪ ሀሳብ ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ስልጠና መስጠት ጀምሯል።
ስልጠናው ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጠሪ የሆኑ ተቋማት፣ የቴክኒክና ሙያን ጨምሮ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ላሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች እየተሰጠ ነው።
የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ስልጠናው የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሰራተኞችን አቅም በመገንባት ለዜጎች ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ያለመ ነው።
አመራሩና ሰራተኛው አገራዊ የለውጥ እሳቤዎችን ከነባራዊ ሁኔታ ጋር በማዛመድ ውጤታማ የሆነ ስራ መስራት እንዲችል ለማድረግ የሚረዳ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ስልጠናው ሰራተኛው ያለውን እውቀትና ክህሎቱ እንዲያጎለብት ከማድረጉ ባለፈ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆን ከማድረግ አንፃር ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ገልፀዋል።
በተጨማሪም በየደረጃው ያለው ሰራተኛ ተናቦና ተቀናጅቶ አገራዊ ተልኮዎችን በብቃት እንዲወጣ ለማድረግ የሚረዳ መሆኑንም አብራርተዋል።
ሚኒስቴሩ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሰው ኃይል አደረጃጃትን የማዘመን፣ ተደራሽነታቸውን የማስፋትና የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ስራም እያከናወነ መሆኑንም አብራርተዋል።
በተጨማሪም የስራ ዕድል ፈጠራው የሃብት ምንጭ እንዲሆን በትኩረት እየሰራ መሆኑንም እንዲሁ።
ከዚህ ውስጥም በርካታ የሚሆኑ ዜጎች ወደስራ ለመሰማራት የሚያስችላቸውን ስልጠና በመስጠት በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ተሰማርተው የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ በኩላቸው፤ ለዜጎች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ተቋማት ሪፎርም እየተካሄደ ነው ብለዋል።
በመዲናዋ ጥራቱን የጠበቀና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንዲችሉም በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
እየተሰጠ ያለው ስልጠና በአዲስ መልክ የተደራጀው ሰራተኛ በእውቀትና በክህሎት የተመሰረተ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የሚያግዘው እንደሆነ ገልፀዋል።
ስልጠናው ዛሬን ጨምሮ ለሚቀጥሉት ሁለት ቀናት እንደሚቆይ ተገልጿል።