በደብረብርሃን ከተማ ለተፈናቃይ ወገኖች ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ምግብ ድጋፍ ተደረገ

164

ደብረ ብርሀን ፤ ሚያዚያ 11/2016 (ኢዜአ)፦ በደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር በመጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ እህል ድጋፍ መደረጉን የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ወይዘሮ ቀለሟ ኃብቴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያና በዘመድ ቤት ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ ሲደረግ ቆይቷል።

ዛሬ በደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ 19ሺህ 210 ወገኖችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የምግብ እህል ድጋፍ ከፌደራል መንግስት መደረጉን ገልፀዋል።

ድጋፉ 26 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው 2ሺህ 882 ኩንታል ስንዴ እና 210 ኩንታል አልሚ ምግብ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይም በእንሳሮና በምንጃር ሸንኮራ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፉ ይቀጥላል ብለዋል።

የድጋፉን ፍታሃዊነት ለማረጋገጥም ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።


 

የድጋፉ ተጠቃሚ አቶ መሐመድ ይመር እንዳሉት፤ እስካሁን በመንግስት፣ መንግስታዊ ባልሆኑ አካላት እና በአካባቢው ነዋሪዎች በተደረገላቸው ድጋፍ ህይወታቸውን ማቆየታቸውን ገልጸዋል።

የዛሬው ድጋፍ ወቅታዊ ችግራቸውን እንደሚያቃልል ጠቁመው፣ በቀጣይም መሰል ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

ወይዘሮ ሀዋ አበባው በበኩላቸው ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው፤ በቀጣይ መንግስት ሰላምን በማረጋገጥ ወደ መጡበት ቄዬ እንዲመልሳቸው ጠይቀዋል።

በሰሜን ሸዋ ዞን ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች እና በዘመድ ቤት የሚኖሩ 89 ሺህ 215 ወገኖች እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም