ባለመላዎቹ ታዳጊዎች

277

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 11/2016 (ኢዜአ)፦ ችግርን ወደ እድል የቀየሩ ባለመላዎቹ ታዳጊዎች

ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆየው የኢትዮጵያ "ስታርት አፕ" አውደ-ርዕይ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በሳይንስ ሙዚየም ለጎብኚዎች ክፍት ተደርጓል።      

በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፍ የተሰማሩ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ''ስታርት አፖች'' በአውደ-ርዕዩ በመሳተፍ ላይ ናቸው። 

አውደ-ርዕዩ የተዘጋጀው በአገሪቱ የሚገኙ ስታርት አፖች ያላቸውን ምርትና አገልግሎት እንዲሁም ፈጠራዎች ተደራሽ ለማድረግ ነው።   

የአቤም ዩዝ አካዳሚ የሰባተኛ ክፍል ተማሪ የሆኑት ጎዶሊያስ ሙሉጌታና ሰላዲን መራዊ የግለሰብ መረጃን ወይንም ሲቪ የሚያደራጅ  ድረ-ገፅ ሰርተው በስታርት አፕ አውደ-ርዕይ  አቅርበዋል።


 

የታዳጊ ጎዶሊያስ ወንድም ስራ ለማመልከት ሲወጣ ''ሲቪ'' ረስቶ ወደቤት በመመለስ ለተጨማሪ ወጪና እንግልት መዳረጉ የዚህ ድረ-ገፅ መልማት መነሻ የሆነ ምክንያት ነው።

ሰዎች ስራን ለመቀጠር የሚያስገቡት የራስ መግለጫ ''ሲቪ'' በእጅ ስልካቸው ኖሮ በማንኛውም ሰዓት ለሚፈልጉት ቀጣሪ ማስገባት የሚያስችል ድረ-ገፅ የሰሩት ታዳጊዎች የአይ ሲ ቲ መምህራቸው ለዚህ ስራቸው እገዛ እንዳደረገላቸው ተናግረዋል። 

ድረ-ገፁ ስለግለሰቡ የትምህርት ደረጃን ጨምሮ፣ አድራሻ፣ ክህሎቶችና የሰዎችን ምስክርነትን ማካተት የሚቻልበት መሆኑን ተናግረዋል። 

ድረ-ገፁ የሰዎችን ብቻ ሳይሆን የድርጅቶችን መረጃ እንዲያስቀምጥ ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑንም ታዳጊዎቹ ያስረዳሉ። 

በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀው አውደርዕይ ላይ መሳተፋቸው ከሌሎች ስታርት አፖች ልምድ እንዲቀስሙና እውቀታቸውን እንዲያዳብሩ እድል የሚፈጥርላቸው መሆኑንም ገልፀዋል።

ስራቸውን እንዲያሳዩ እድል ስለተፈጠረላቸውና እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ እገዛ ላደረጉላቸው አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።   

በቀጣይም ችግር ፈቺ የምርመር ስራዎችን በመስራት አገራቸውን ለመጥቀም እንደሚሰሩ ገልጸዋል።       

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም