20ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ በዋሽንግተን ዲሲ ተካሔደ

236

 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 11/2016(ኢዜአ)፦ 20ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ በወቅቱ የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ሊቀመንበር የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ መሪነት በዋሽንግተን ዲሲ ተካሒዷል።

ሚኒስትሩ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) እና ዓለም ባንክ ስብሰባ ጎን ለጎን 20ኛውን የምስራቅ አፍሪካ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ መርተዋል።


 

በውይይቱም የአፍሪካ ቀንድ ሃገራት የገንዘብ ሚኒስትሮች፣ የልማት አጋሮች የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የአውሮፓ ህብረት የጀርመን እና የእንግሊዝ ተወካዮች መሳተፋቸው ተገልጿል።

ሚኒስትሩ በውይይቱ ላይ እንደ አረብ ባንክ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ልማት ፣የሳኡዲ ልማት ፈንድ፣ ጃፓንና የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ያሉ አጋሮችን ተሳትፎ አመስግነዋል።

አቶ አህመድ አያይዘውም ሌሎችም በአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ማዕቀፍ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢኒሼቲቩ ባለፉት አምስት አመታት ሀብት በማሰባሰብ ረገድ ስኬታማ እንደነበር አስታውሰው፤ ይህ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አፅንኦት ሰጥተዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ኢንሼቲቭ ሰባት የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን በአባልነት አካትቶ በፈረንጆቹ 2019 የተመሰረተ ሲሆን በቀጠናው ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ለማጠናከር እየሰራ እንደሚገኝ ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም