መንግስት ለሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ተግባራዊነት በቁርጠኝነት ይሰራል-- ተስፋዬ በልጅጌ

437

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 11/2016 (ኢዜአ)፦ መንግስት ለሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ተግባራዊነትና ውጤታማነት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ገለጹ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤን ጨምሮ የዴሞክራሲ ተቋማት አመራሮችና ሌሎች በተገኙበት በሽግግር ፍትህ ፖሊሲና የፌደራል የአስተዳደር ስነ-ስርአት አዋጅ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ በዚሁ ጊዜ የተለያዩ የዓለም አገራት ከተወሳሰበ ችግርና ቀውስ ለመውጣት የሽግግር ፍትህን መፍትሄ አድርገው መጠቀማቸውን አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያም በቀደሙ ስርዓቶች የተፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ በታሪክ ምክንያት የሚነሱ አለመግባባቶች፣ የዴሞክራሲ ስርዓት አለመጎልበት፣ ለዘመናት የተከማቹ የፖለቲካ ቀውሶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ለእነዚህ ችግሮች እልባት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር የሚመጋገብና ሂደቱን የሚያሳልጥ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

መንግስት ፖሊሲው እንዲዘጋጅ ከማድረግ ጀምሮ ቁርጠኛ የፖለቲካ አቋም መውሰዱን ገልጸው፤ይህም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አብራርተዋል፡፡ 

የአሁኑ ትውልድ ችግሮችን ቀርፎ ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምእራፍ የማሸጋገር ኃላፊነት እንዳለበትም ነው የተናገሩት፡፡  

ፖሊሲ ለረዥም ጊዜ ስር የሰደዱ ችግሮችን በመፍታት ከችግር መውጫ አንዱ መሳሪያ መሆኑንም አጽኖት ሰጥተው  ተናግረዋል።

የትናንት ቁርሾዎችን በእርቀ ሰላምና ይቅርታ በመዝጋት ለነገ ትውልድ የተረጋጋችና ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት አገር ማስተላለፍ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

በዚህ ረገድ መንግስት የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ለፖሊሲው ተፈጻሚነት በጋራ መስራት እንደሚገባ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የፖሊሲው ወቅታዊነትን በሚመለከትም ከተሳታፊዎች ጥያቄ ቀርቧል፡፡

 አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በምላሻቸው አገራዊ የሆኑ ችግሮች በይደር የሚታለፉ አለመሆናቸውን ጠቅሰው፤ ችግሮቹን  በአንድነት ለመፍታት ጊዜው አሁን መሆኑን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ገለልተኛ ተቋማትን በማደራጀት ነጻና ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ ለማድረግ የተጀመረው ስራ ለፖሊሲው ተፈጻሚነትም አስቻይ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥርም አንስተዋል።

በሌላ በኩል የፌደራል የአስተዳደር ስነ-ስርአት አዋጅ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አዋጁ አጠቃላይ የተጀመረው ለውጥ ስራ አካል መሆኑን በመጥቀስ ይህም የአሰራር ማነቆዎችን በመፍታት፣ አደረጃጀትን በማስተካከል፣ አገልግሎትን በማሻሻል ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ነው ያሉት።

አዋጁ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ የተቋማት ኃላፊዎችና ሙያተኞች ተግባራዊነቱ ላይ በልዩ ትኩረት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም