የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ሁሉም በትብብር ሊሰራ ይገባል-አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

106

ጋምቤላ ፤ ሚያዚያ 11/2016 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል የትምህርት ቤቶችን ደረጃና ግብዓት በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።

የክልሉ የ2016 በጀት ዓመት  የዘጠኝ  ወራት የእቅድ  አፈጻጸም  ግምገማ ዛሬ  በጋምቤላ  ከተማ  ተካሄዷል ። 


 

ርዕሰ  መስተዳድሩ  በግምገማ  መድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤ የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማትና ግብዓት በማሻሻል የትምህርት  ጥራትን  ለማስጠበቅ የሁሉም ባለድርሻ  አካላት ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል። 

''የትምህርት  ቤቶችን  ደረጃና ግብዓት በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ "ትምህርት  ለትውልድ " በሚል አገር አቀፍ ንቅናቄ ወደ ስራ የተገባ ቢሆንም እንደ ክልል የተከናወኑት ተግባራት በቂ አይደሉም'' ብለዋል። 

በክልሉ ትምህርት ቤቶችን ተደራሽ በማድረግ ረገድ የተሻለ አፈፃፀም ቢኖርም ትምህርት ቤቶቹ የደረጃና የግብዓት ችግር  ያለባቸው መሆኑን ገልጸዋል ።

በመሆኑም በዘርፉ የተጀመሩ የንቅናቄ ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የታለመውን ግብ ለማሳካት የአመራሩ፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና የመላው ማህበረሰብ  ተሳትፎ ሊጠናከር  እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል ። 

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ላክደር ላክባክ በበኩላቸው ባለፉት ዘጠኝ ወራት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻልና በግብዓት ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል። 

በክልሉ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተጀመረው የምገባ መርሃግብር የተማሪዎችን መጠነ ማቋረጥ በመቀነስ ረገድ ፋይዳዉ የጎላ መሆኑን ገልፀዋል። 

ይሁን እንጂ የምገባ መርሃ ግብሩን ሳይቆራረጥ ለማስቀጠል እንዲቻል የመንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እገዛ ሊጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል። 

የግምገማ መድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ከማሻሻል ጎን ለጎን የመምህራንን አቅም ማጎልበት እንደሚገባም ሃሳብ ሰንዝረዋል። 

በግምገማ መድረኩ ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮችን ጨምሮ የዘርፉ ባለሙያዎችና የወላጅ መምህራን ህብረት ኮሚቴዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም