የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለ1 ሺህ 460 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

143


ባህር ዳር   ፤ ሚያዝያ 11/2016 (ኢዜአ)፦ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የይቅርታ አዋጁን ያሟሉ 1 ሺህ 460 የህግ ታራሚዎች በይቅርታ እንዲፈቱ ማድረጉን የክልሉ ፍትህ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ጎሽም ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ የክልሉ መንግስት በበጀት ዓመቱ ለ2ኛ ጊዜ በሰጠው ይቅርታ ከሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ይቅርታ የተደረገላቸው 1ሺህ 460 የህግ ታራሚዎች ከእስር እንዲፈቱ ወስኗል።

የይቅርታ ተጠቃሚ ከሆኑት የህግ ታራሚዎች መካከል 29ኙ ሴቶች ሲሆኑ 1ሺህ 431ዱ ደግሞ ወንዶች መሆናቸውን አመልክተዋል።

የህግ ታራሚዎቹ የይቅርታ ተጠቃሚ የሆኑት ይቅርታ በማያስከለክሉ ወንጀሎች ተሳትፈው በማረሚያ ቤት የቆዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ተጠቃሚዎቹ ከግል ተበዳይ ጋር የታረቁና የካሱ፣ በጤና ችግርና በዕድሜያቸው የገፉ፣ አብዛኛውን የእስር ጊዜ ያጠናቀቁ እንዲሁም በቆይታቸው የባህሪ ለውጥ ማምጣታቸው የተረጋገጠላቸው መሆኑንም አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ በዘር ማጥፋት፣ በአስገድዶ መድፈር፣ ሰውን አስገድዶ በመሰወር፣ ከ10 ዓመትና ከዛ በላይ በሚያስቀጣ የሙስና ወንጀል በፈፀሙ፣ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል የተሳተፉ እንዲሁም በሽብርተኝነትና በመሰረተ ልማት ማውደም ወንጀል የተሳተፉ ታራሚዎች የይቅርታው ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ገልጸዋል።

በፈፀሙት ወንጀል ታርመው የይቅርታው ተጠቃሚ የሆኑ የህግ ታራሚዎችም ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ የበደሉትን ህብረተሰብ በልማት ሊክሱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ህብረተሰቡም የህግ ታራሚዎቹ በፈጸሙት ጥፋት የተፀፀቱና በአግባቡ ታርመው የወጡ መሆኑን በመረዳት ከእስር የተለቀቁ ታራሚዎች ኑሯቸውን በተረጋጋ ሁኔታ እንዲመሩ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል። 

የክልሉ ምክር ቤት ቀደም ሲል የይቅርታ ተጠቃሚ ሆነው ከማረሚያ ቤት ከወጡ በኋላ ሦስት ዓመት ሳይሞላቸው ሌላ ወንጀል ፈፅመው የተገኙ አምስት የህግ ታራሚዎች ቀደም ሲል የተሰጣቸው ይቅርታ እንዲሰረዝ መወሰኑንም አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም