በአዲስ አበባ ያሉ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጣቸውን የማዘመንና ተደራሽነታቸውን ማስፋት ላይ ትኩረት ተሰጥቷል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

113

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 11/2016 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ያሉ  ተቋማት አገልግሎት አሰጣጣቸውን የማዘመንና ተደራሽነታቸውን የማስፋት ስራ እንዲያጎለብቱ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስሩ ለሚገኙና ከክፍለ ከተማ እስከ ወረዳ ላሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚውሉ 150 የኤሌክትሪክ  ተሽከርካሪዎችን አስረክቧል፡፡


 

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተሽከርካሪዎቹን ቁልፍ ለተቋማቱ ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት ተቋማት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል።

በተለይም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን መፍታት  የሚያስችሉ ግብዓቶችን ማቅረብ ላይ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።

ዛሬ በከተማ አስተዳደሩ ስር ለሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተከፋፈሉትና በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት አሰጣጡን በማቀላጠፍ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።

በተለይም ተቋማቱ ያሉባቸውን ክፍተቶች በመሙላት አቅማቸውን ለማሳደግና ለማብቃት ያለመ ስለመሆኑም ከንቲባዋ አብራርተዋል።

ተሽከርካሪዎቹ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ባሻገር በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ጉልሀ ሚና እንደሚኖራቸውም አንስተዋል።

በተለይም ከተማ አስተዳደሩ አዲስ አበባን ጽዱ፣ አረንጓዴና ለኑሮ ተስማሚ ለማድረግ እያከናወነ ላለው የልማት ስራ በእጅጉ የሚያግዙ ናቸውም ብለዋል።

በመሆኑም በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ያሉ አገልጋዮች ስራቸውን በአግባቡና በኃላፊነት በመወጣት የተጣለባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል።

ለህዝብ አገልግሎት እንዲውሉ ታልመው በግዢ የተላለፉት እነዚህን ተሽከርካሪዎችንም በአግባቡ ሊጠቀሙ እንደሚገባም ከንቲባዋ አጽንኦት ሰጥተዋል።

መኪኖቹ ከበላይነህ ክንዴ ግሩፕ በአገር ውስጥ የተገጣጠሙና በግዥ የቀረቡ መሆኑን ተገልጿል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም