የረጅም ዘመን የሃይማኖት ታሪክ ባላት ኢትዮጵያ የሚገኙ ሃይማኖት አባቶች ለቀጣናው ሰላም መስራት ይጠበቅባቸዋል አብድረህማን እስማዔል

67

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 11/2016 (ኢዜአ)፦"የረጅም ዘመን የሃይማኖት ታሪክ ባላት ኢትዮጵያ የሚገኙ ሃይማኖት አባቶች  ከአገር ውስጥ ባለፈ ለቀጣናው ሰላም መስራት ይጠበቅባቸዋል'' ሲሉ የኬንያ የሃይማኖት ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አብድረህማን እስማዔል ተናገሩ፡፡ 

በየትኛውም የአለም ክፍል የህዝቦችን አብሮነት፣ መቻቻል፣ ፍቅርና ሰላም በማረጋገጥ ረገድ የሃይማኖት አባቶች ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው።

የአንድን አገር ሰላም የማረጋገጥ ሃላፊነት በዋናነት የመንግስት ቢሆንም ዜጎች ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን በአግባቡና ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲወጡ ከሚያግዙ አካላት መካከል የሃይማኖት አባቶች ግንባር ቀደም ናቸው፡፡

የሃይማኖት አባቶች በተለያዩ ቦታዎች የሚታዩ የፀጥታ መደፍረስና አለመረጋጋቶችን በሰላም ለመፍታት ሚናቸው የጎላ ነው፡፡

በተለይ በምስራቅ አፍሪካ የሚከሰቱ የእርስ በእርስ ግጭቶች ለሰዎች ህይወት መጥፋት እና ለንብረት መውደም ምክንያት እንዳይሆኑ በቀጣናው አገራት ያሉ የሃይማኖት አባቶች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። 

በአካባቢው የሚታዩ ግጭቶች ተወግደው በቀጣናው ሰላም እንዲሰፍን የእምነት አባቶች ሚና ምን ሊሆን ይገባል ሲል ኢዜአ ከኬንያ የሃይማኖት ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አብዱራህማን እስማዔል ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት "የሃይማኖት አባቶች ሰዎች እንዴት እርስ በእርስ ተዋደውና ተፋቅረው መኖር እንዳለባቸው የማስተማር ኃላፊነት አለባቸው"፡፡

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የእምነት አባቶች ጥላቻን በማስወገድ ሰዎች እርስ በእርስ ተዋደው እና ተፋቅረው እንዲኖሩ፣ እንዲሁም ልማት እንዲረጋገጥ በጋራ እያደረጉት ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስኬት ለአፍሪካ አገራት በተለይ ደግሞ የምስራቅ አፍሪካ ስኬት ነው ያሉት  ዋና ዳይሬክተሩ፤ ሃይማኖት አባቶች ለቀጣናው ሰላም መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በሰዎች መካከል የሚታየውን ጥላቻ በማስወገድ ፍቅር እንዲጎለብት እያደረጉት ያለውን ጥረት አድንቀው፤ በቀጣይም ይኽው ጥረታቸው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉም  ተናግረዋል ፡፡ 

በርካታ አማኞች ባሉባት ኢትዮጵያ የሃይማኖት አባቶች ስለሰላም አብዝተው በመስበክ ለአለም ምሳሌ ሊሆኑ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ፣ የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖቶች ለረጅም ዘመናት በሰላምና በፍቅር የሚኖሩባትና እየኖሩባት ያለች ታላቅ አገር መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡

ነብዩ መሐመድ ተከታዮቻቸው ችግር ውስጥ በወደቁበት ወቅት ወደ ኢትዮጵያ ሂዱ ማለታቸው የሁለቱን ሃይማኖቶች የረዥም ጊዜ ቁርኝት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

ህብረ ብሔራዊነትን የተላበሰችው ታላቋ ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን ታስፈልጋለች ይህችን ታላቅ ሀገር ለመገንባት ተባብሮ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ይህን ማድረግም ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ባለፈ ጠቀሜታው ለቀጣናው አገራት ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም