ኢትዮጵያ ለስታርት አፕ የሰጠችው ትኩረት የዲጅታል ኢኮኖሚ ግንባታ ርዕይና ተስፋዋን የሚያሳካ ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

206

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 11/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለስታርት አፕ የሰጠችው ትኩረት የዲጅታል ኢኮኖሚ ግንባታ ርዕይና ተስፋዋን የሚያሳካ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በሳይንስ ሙዚየም የተከፈተውን የስታርት አፕ ኢትዮጵያ አውደ ርዕይ ጎብኝተዋል።


 

በጉብኝታቸውም ኢትዮጵያን በብዙ መልኩ የሚጠቅሙ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሀሳቦችን መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ሀገርን ሊያሳድጉ የሚችሉ የፈጠራ ሀሳቦች ያሏቸው ወጣቶችና ታዳጊዎችን የኢትዮጵያ እድገት ተስፋዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ መንግስት ይህንን በመገንዘብ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት መስጠቱን አንስተዋል።


 

10 ዓመቱ የልማት እቅድ የገቢና ወጪ ምርቶችን ለማመጣጠንና የቴክኖሎጂ ፈጠራን ለማሳደግ የተያዘውን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት ስታርት አፖች ሚናቸው ትልቅ ነው ብለዋል።

መንግስት ስታርት አፖችን ለማጠናከር እየሰራ ስለመሆኑ አንስተው፤ ለአብነትም ምርቶቻቸውን ገዝቶ መጠቀምን የሚያበረታታ እንዲሁም የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያደርጉ የፖሊሲ አቅጣጫዎችንና የህግ ማዕቀፎችን ወደ ስራ ማስገባቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂና በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ብዙ ተስፋ እንዳላት ገልጸው፥ ኢትዮ ቴሌኮም አካታች የዲጅታል ኢኮኖሚ ስርዓትን በማሳለጥ ትላልቅ ስራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።

በተለይ በቴሌ ብር አገልግሎት አነስተኛ ብድሮችን በማቅረብ እና አርሶና አርብቶ አደሩን ጭምር የሚያሳትፉ ማዕቀፎችን በመተግበር ትልቅ እምርታ እያስመዘገበ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በሰው ሰራሽ አስተውሎትና በቴክኖሎጂ ፈጠራ ያሉ ጅምሮች ኢትዮጵያ ያላትን ግዙፍ ራዕይ ማሳካት እንደሚቻል የሚያሳዩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የመንግስት አገልግሎትን ለማዘመን ትልቅ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸው፤ በተለይም ቴክኖሎጅን ያወቀና የአገልጋይነት መንፈስ ያለው የሰው ኃይል ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል

ኢትዮጵያ በቀጣናው ብሎም በአፍሪካ የዲጅታል ኢኮኖሚ ማዕከል ለመሆን እየሰራች መሆኑንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ሀገራዊ የብልፅግና ጉዞን ለማሳካት በየክልሎች ያሉ ስታርት አፖችን ሁሉም ሊያበረታታ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም