አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ተጠቃሚና ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ ነው

115

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 11/2016 (ኢዜአ)፦  የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ተጠቃሚ እና ውጤታማ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ፋይናንስ ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ ለአምራች ኢንተርፕራይዞች የንግድ ልማት አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል።

በዚህ መነሻነት ትግበራውን ለማከናወን ከተቋሙ ውል የወሰዱት ኮንሶልና አይ ከርቭ ኮንሠልት የትግበራ ዕቅዳቸውን ለባለድርሻ አካላት አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።


 

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለባቸው ንጉሴ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የንግድ ልማት አገልግሎት ለአምራች ኢንተርፕራይዞች ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

ይህን ተከትሎ ዘርፉ ለአምራች ኢንተርፕራይዞች ካለው ጠቀሜታ አንፃር በልዩ ትኩረት እየተደገፈ መሆኑን በማንሳት የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ስትራቴጂ እንዲኖረው ለማስቻል ተቋማቸው ከአማካሪ ድርጅቶቹ ጋር በመተባበር እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል።

ፕሮጀክቱ የአምራች ኢንተርፕራይዝ ዘርፉን ለመደገፍ የተቀረጸ መሆኑን ተከትሎ የንግድ ልማት አገልግሎትን በስፋት ለማስተዋወቅና ተደራሽ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስረድተዋል።

ይህ የንግድ ልማት አገልግሎት የልዩ ልዩ ሠነዶች ዝግጅት፣ ስልጠና፣ የማማከር ስራዎች፣ ጥናትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ጨምሮ 11 ያህል ተግባራት የሚከናወኑበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ዕቅዱ ስልጠናዎች ምን አይነት መሆን አለባቸው፤በምን መልኩ መሰጠት አለባቸው፤ የሚለውን የሚያመላክት ስለሆነ ፤ ውጤታማ እንዲሆን ድጋፋቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል፡፡

ስልጠናው በአለም ባንክ የሚደገፍ ሲሆን የአምራች ኢንተርፕራይዞችን አቅም በመገንባትና  አሰራራቸውን በማሻሻል ውጤታማ እንዲሆኑ ለማገዝ ያስችላል ብለዋል ፡፡

የንግድ ልማት አገልግሎት ቡድን መሪ ዶክተር ሃብታሙ ደመራ በበኩላቸው፤ የአምራች ኢንተርፕራይዞችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ስልጠና በመስጠት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ስልጠናው የኢንተርፕራይዞችን የውጭ ገበያ ድርሻ ለማሳደግ ፤ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካትና የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ድርሻ ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ለ500 ኢንተርፕራይዞች እና ለ50 ባለሙያዎች ተገቢውን ስልጠናና ቴክኒካል ድጋፍ  ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም