በአማራ ክልል የሌማት ትሩፋት መረሃ ግብር የዜጎችን ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እያገዘ ነው

112

ደሴ፤  ሚያዚያ 11/2016(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል በንቅናቄ የተጀመረው  የሌማት ትሩፋት  መረሃ ግብር የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እያገዘ መሆኑን የክልሉ እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ፓኬጅ የአሰልጣኞች ስልጠና የማጠቃለያ መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ ተካሂዷል፡፡

የክልሉ እንስሳት ዓሳ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ነጋ ይስማው በወቅቱ እንዳሉት፤ በዘርፉ የተሻሻለ አሰራርና ቴክኖሎጂ በመጠቀም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው፡፡

ለዚህም በንቅናቄ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መረሃ ግብር በክልሉ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በገጠርና በከተሞች ህብረተሰቡ በአነስተኛ ስፍራና በቀላሉ በእንስሳት ማድለብ፣ ዶሮ እርባታ፣ ንብ ማነብ፣ በወተት ልማትና ዓሳ እርባታ ላይ በመሰማራት የአቅርቦት እጥረት እንዳይኖር እያገዘ ነው ብለዋል።

በዚህም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።

መረሃ ግብሩን ለማስፋትም የአዲስ አሰራር ፓኬጅ ስልጠና መሰጠቱን ጠቁመው፤ ዜጎች በአዋጭ ዘርፍ ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የባለሙያ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

በደቡብ ወሎ ዞን እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የእንስሳት እርባታ ባለሙያ ወይዘሮ ሽብሬ መርሻ በበኩላቸው፤ህብረተሰቡ በሌማት ትሩፋት መረሃ ግብር ላይ በመሳተፍ  ራሱን ከመቻል ባለፈ ለገበያ እያቀረበ ተጠቃሚ እየሆነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በተለይም እንቁላል፣ ወተት፣ አትክልትና መሰል ምርቶችን ህብረተሰቡ በቀላሉ በማምረት እንዲጠቀም እድል መፍጠሩን ተናግረዋል።


 

'የሌማት ትሩፋት በቀላሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ  ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን  የገለጹት ደግሞ  በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን እንስሳትና ዓሳ ሀብት ጽህፈት ቤት እንስሳት እርባታ ቡድን መሪ አቶ በሪሁን ተፈራ ናቸው፡፡

በዚህም ህብረተሰቡ በአካባቢው የማር፣ የወተት፣ የእንቁላል፣ የስጋና የሌሎችንም ምርቶች በቀላሉ እያገኘ  የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም እያገዘ ነው ብለዋል፡፡

ለአራት ቀናት በተሰጠው የፓኬጅ ስልጠና የምስራቅ አማራ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች የዘርፉ የአመራር አባላትና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም