የግሉ ዘርፍ በዲጂታል ምህዳሩ ላይ ያለውን ተሳትፎ በማጎልበት ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው- የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

129

አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 11/2016 (ኢዜአ)፦የግሉ ሴክተር በዲጂታል ምህዳሩ ላይ  ያለውን ተሳትፎ  በማጎልበት ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ይሽሩን ዓለማየሁ ገለፁ።

 ራይድ ትራንስፖርት እና ታዋቂው ዓለም አቀፍ የዲጂታል ክፍያ ተቋም ቪዛ በኢትዮጵያ የትራንስፖርት ክፍያን ለማቀላጠፍ የሚያስችል ጥምረት መፍጠራቸውን አስታወቀዋል።

ጥምረቱ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የውጭ አገር ዜጎች እና ዳያስፖራዎች የቪዛ ካርዳቸውን ብቻ በመጠቀም የትራንስፖርት ክፍያቸውን እንዲያከናውኑ የሚያስችል ነው፡፡ 

ይህም ጎብኚዎች አስተማማኝና ቀልጣፋ ትራንስፖርት በማግኘት በኢትዮጵያ አስደሳች ቆይታ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ይሽሩን አለማየሁ “ዲጂታል ኢትዮጵያ”ን እውን ለማድረግ ከሚከናወኑ ስራዎች መካከል ዲጂታል ክፍያ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የዲጂታል ክፍያ ስርዓትም የተቀላጠፈና ዘመናዊ አሰራር ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዝ ነው ያብራሩት፡፡

ለዲጂታል ኢትዮጵያ ግንባታ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ መንግስት የዲጂታል ምህዳሩን ምቹ ማድረግ ጨምሮ የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

የሃይብሪድ ዲዛይንስ እና ራይድ መስራች ሳምራዊት ፍቅሩ፤ ጥምረቱ "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" እውን ለማድረግ እየተከናወነ ካለው ስራ ጋር የሚጣጣም መሆኑን ጠቁመዋል፡፡


 

ጥምረቱ ኢትዮጵያን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ጥሬ ገንዘብ ሳይጠቀሙ በቪዛ ካርዳቸው ብቻ አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት፡፡

በኢትዮጵያ የቪዛ ዳይሬክተር ያሬድ እንዳለ በበኩላቸው፤ ቪዛ የተቀላጠፈ እና አስተማማኝ የዲጂታል ክፍያን ለሁሉም እና በሁሉም ቦታ ለማዳረስ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 


 

በመሆኑም ከራይድ ጋር የተጀመረው ጥምረት  የኢትዮጵያን የጉዞ እና ቱሪዝም ዘርፍ ለማዘመን ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይም የቪዛ ክፍያ ስርዓትን በሌሎች አገልግሎቶችም ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራም ነው የገለጹት፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም