ደም መለገስ ከህሊና እርካታ ባለፈ የሰዎችን ህይወት ይታደጋል---ደም ለጋሾች

183

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 11/2016 (ኢዜአ)፦ ደም መለገስ ከህሊና እርካታ ባለፈ የሰዎችን ህይወት  እንደሚታደግ  ከ90 ጊዜ በላይ ደም የለገሱ በጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾች ተናግረዋል፡፡

ደም መለገስን ሳስብ ቀድመው ወደ አእምሮዬ የሚመጡት በአንድ ወቅት ታሪካቸውን ያነበበኩት ወይዘሮ ያለምእሸት ውቡ ናቸው፡፡

ወይዘሮዋ በወሊድ ወቅት ብዙ ደም ፈሷቸው ከሞት አፋፍ ተመልሰዋል፡፡

በወቅቱ ቤተሰቦቻቸው ደም ለመለገስ ፈቃደኛ ባልነበሩበት ጊዜ ደም ማን እንደለገሳቸው እና እንዴት ሕይወታቸው እንደተረፈ እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን በርካታ ደጋጎች በፍቃደኝነት በሚለግሱት ደም የማያውቋቸውን የሰብዓዊ ወገኖቻቸውን ህይወት ታድገዋል፡፡


 

ከነዚህ መካከል የ51 ዓመቱ ጎልማሳ አቶ ዳዊት ተስፋዬ አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ዳዊት ላለፋት 31 ዓመታት በበጎ ፈቃደኝነት ደም በመለገስ የበርካታ ወገኖቻቸውን ህይወት መታደግ መቻላቸው የህሊና እረፍት እንደሰጣቸው ይናገራሉ።

በሸገር ከተማ ፉሪ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው አለም ገና አካባቢ ተወልደው ያደጉት አቶ ዳዊት ከ1983 ዓ.ም አንስቶ በፍቃደኝነት ደም መለገስ መጀመራቸውን ያስታውሳሉ። 

በወቅቱ ከአዲስ አበባ ቀይ መስቀል ወጣቶች ጋር ሲንቀሳቀሱ በርካታ ሰዎች በደም እጦት ህይወታቸው ሲያልፍ መመልከታቸው ደም ለመለገስ እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።

በዚህም ላለፋት 31 ዓመታት በየሶስት ወሩ ያለማቋረጥ ደም መስጠታቸውንና በቅርቡም ለ97ተኛ ጊዜ ደም እንደለገሱ ገልጸዋል፡፡ 

ደም መለገስ ከህሊና እርካታ ባለፈ የሰዎችን ህይወት ለመታደግና ለጤና በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት ተሞክሮአቸውን አጋርተዋል።

ደም መለገስ የሰዎችን ህይወት ማትረፍ የሚቻልበት ቅዱስ ተግባር መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ለ91ኛ ጊዜ ደም  የለገሱት አቶ መስፍን አዲሴ  ናቸው።

''ዕድሜና ጤና እስከሰጠኝ ድረስ ደም መለገሴን አላቋርጥም፡ ምክንያቱም ደም መለገሴ ምንም አይነት የጤና ጉዳት አያመጣብኝም'' በማለት ያለፉበትን አስታውሰዋል፡፡

ህብረተሰቡ የእነሱን ተሞክሮ አጽንኦት በመስጠት በየሶስት ወሩ በቋሚነት ደም በመለገስ የወገኖቹን ህይወት እንዲታደግ  ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ሀብታሙ ታዬ በበኩላቸው ባለፋት ዘጠኝ ወራት 315 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ 248 ሺ ዩኒት ደም መሰብሰቡን አስታውቀዋል።


 

ለአፈጻጸሙ ማነስ በአንዳንድ አካባቢዎች የነበሩ የጸጥታ ችግሮችና ወቅቱ የጾም ጊዜ መሆኑን አንስተዋል።

የደም ለጋሾች ቁጥር በሚፈለገው ልክ አለማደጉን ተከትሎ የደም እጥረት ያጋጠመ ሲሆን፤  ህብረተሰቡ የጉዳዩን አንገብጋቢነት በመረዳት ደም እንዲለግስ ጠይቀዋል ።

በተለያዩ የህክምና ተቋማት ደም የሚፈልጉ በርካታ ህሙማን በመኖራቸው ህብረተሰቡ ደም በመለገስ የወገኖቹን ህይወት እንዲታደግም ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

 ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ  በተለያዩ ሥፍራዎች ድንኳን በመትከል ደም የማሰባሰብ ስራ ስለሚጀምር ሁሉም ዜጋ በበጎ ፍቃድ ደም እንዲለግስ ጠይቀዋል፡፡

የጾም ወቅቶች ፤ትምህርት ቤቶች ሲዘጉና የአደባባይ በዓላት በሚኖሩበት ወቅት የደም እጥረት እንደሚከሰት በማስታወስ እጥረቱን ለማስወገድ ህብረተሰቡ ደም እንዲለግስ ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም