አቶ አደም ፋራህ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ጋር ተወያዩ

331

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 11/2016 (ኢዜአ)፦ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣዎ ዢዋን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸው የጋራ ተጠቃሚነትን ለማስፋት፣ የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር እንዲሁም የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስፋት ዙሪያ መክረዋል፡፡

አቶ አደም ፋራህ የኢትዮ-ቻይና ዘመናትን የተሻገረ ወዳጅነት ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠሉንና የቻይናው ኮሙኒስት ፓርቲ አጋርነትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

ከዚህ በፊት በሁለቱ ፓርቲዎች ስምምነት መሰረት በትምህርት፣ በስልጠና እንዲሁም በተሞክሮና ልምድ ልውውጥ አብሮ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ስምምነት መደረጉን አንስተዋል፡፡

በቅርቡ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ተሳታፊ የሆኑበት የልዑካን ቡድን ውጤታማ ቆይታ አድርጎ መመለሱም የዚህ ስምምነት አካል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ለልዑካን ቡድኑ ለተደረገው አቀባበልና ስኬታማ የቆይታ ጊዜ ያላቸውን ምስጋና ገልጸዋል።

በቀጣይም የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነቶች በመሰል የስልጠናና የልምድ ልውውጥ መርሐ ግብሮች ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብልፅግና ፓርቲ ፍላጎቱ እንደሆነ ማብራራታቸውን ከፓርቲው የተገኘው  መረጃ ያመላክታል፡፡

አምባሳደር ዣዎ ዢዋን በበኩላቸው የብልፅግና ፓርቲ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ እየሰራቸው ያሉ ውጤታማ ስራዎችን አድንቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ የቻይና ጠንካራ ስትራቴጂክ አጋር መሆኗን ጠቅሰው ይህ ግንኙነት በፓርቲ ለፓርቲም ሆነ በመንግስታዊ ወዳጅነት ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲያድግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም