ዜጎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትና የተቀራረበ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የምሁራን ሚና ከፍተኛ ነው-ዶክተር ከይረዲን ተዘራ

240

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 11/2016 (ኢዜአ)፦ ዜጎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትና የተቀራረበ ግንዛቤ እንዲይዙ ምሁራን የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከይረዲን ተዘራ ገለጹ።

የሰላም ሚኒስቴር "ዘመኑን የዋጀ አርበኝነት ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር አቀፍ የንቅናቄ መድረክ ያስጀመረ ሲሆን በእለቱ ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተወካዮች ጋር ውይይት ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከይረዲን ተዘራ ከዚህ ቀደም "አድዋን ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ" በሚል መሪ ሃሳብ ከ 40 በላይ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ውይይት መካሔዱን አስታውሰዋል።

በመድረኮቹ የጋራ ማንነት ፣ እሴት እና ሀገራዊ ጥቅም ላይ ያተኮሩ ስኬታማ ውይይቶች መደረጋቸውን በማስታወስ ኩነቱ በቀጣይ ለሚካሔዱ የንቅናቄ መድረኮች ትልቅ ግብአት የተገኘበት መሆኑን ተናግረዋል።

ምሁራን መሰል ሀሳቦችን በማውረድ፣ በማወያየት እና በማዳበር በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትና የተቀራረበ ግንዛቤ እንዲኖር ለማስቻል የላቀ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

"ዘመኑን የዋጀ አርበኝነት ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ ይፋ የተደረገው ንቅናቄም በተመሳሳይ መልኩ የሚተገበር መሆኑን ተናግረዋል።

በሁሉም ዘርፍ ለሀገር ልማትና ብሄራዊ ጥቅም ታማኝ ሆኖ መስራት ከዜጎች የሚጠበቅ ተግባር በመሆኑ በተለይም ምሁራን በዚህ ረገድ ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲዎች የተቋቋሙ ፎረሞች በዚህ ረገድ ከፍ ያሉ ሀሳቦችን በማንሳት ውይይት በማድረግ ለንቅናቄው ስኬት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ ምሁራን በበኩላቸው ለውይይቱ የሚረዱ አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሀገሪቱ ያለው የውይይት ባህል እንዲዳብርና በመነጋገር የሚያምን ትውልድ እንዲፈጠር የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

በዚህ ረገድ ምሁራን ግንባር ቀደም ሚና መጫወት እንዳለባቸው ገልጸው ውይይቶቹ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ የተሳኩ እንዲሆኑ  በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም