በመዲናዋ እየተተገበረ የሚገኘው የወንዞች ዳርቻ ልማት የመዲናዋን ወንዞች ትንሳኤ አብስሯል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

260

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 11/2016(ኢዜአ)፦ ካለፉት አምስት አመታት ጀምሮ በመዲናዋ እየተተገበረ  የሚገኘው የወንዞች ዳርቻ ልማት የመዲናዋን ወንዞች ትንሳኤ ያበሰረ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ "ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ" በሚል መሪ ሃሳብ ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት ንቅናቄ አስጀምረዋል።


 

ንቅናቄው የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ጽዱ አዲስ አበባን እውን ለማድረግ አላማ የያዘ ነው፡፡

በመርኃ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቡዜና አልከድር፣ የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ስራአስኪያጅ ድዳ ድሪባ፣ የካቢኔ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በዚሁ ወቅት የመዲናዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዳሉት፤ አዲስ አበባ እንድትመሰረት ምክንያት የሆናት የተፈጥሮ ሀብቷና መልከ ብዙ የአየር ንብረቷ ነው።

ይሁን እንጂ እነዚህን የተፈጥሮ ሀብቶች በአግባቡ መጠበቅ ባለመቻሉ መዲናዋ ለከፍተኛ ብክለት ተዳርጋለች ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት ጠቁመዋል፡፡

እነዚህ ጉልህ ችግሮች በከተማዋና በዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች ጤናን የሚያውኩ ጉዳቶችን እያስከተሉ ነው ብለዋል።

ይህን ተከትሎ ባለፉት አምስት ዓመታት ችግሮቹን ለማቃለልና የከተማዋን ስነ-ምሕዳር ለማሻሻል የሚረዱ ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራቱን አብራርተዋል።

በዋናነትም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት እየተተገበረ የሚገኘው የወንዝ ዳርቻ ልማት የመዲናዋን ወንዞች ትንሳኤ ያበሰረ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ የነበረውን የመዲናዋን የደን ሽፋን መታደግ እንዳስቻለ አስታውቀዋል።

እነዚህ ስራዎች ዘላቂ ልማትን ከማረጋገጥ አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን  አመላክተዋል።

በከተማዋ ያለው የፍሳሽ ማስወገጃ ስርአት በአብዛኛው ከወንዞች ጋር የተገናኘ በመሆኑ በቅርቡ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ችግሩን  ለመፍታት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ረጅም ጊዜ ያገለገሉ ተሽከሪዎች በአየር ንብረት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደሩ መሆኑን በመጠቆም በታዳሽ ሀይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል የወጣው ፖሊሲ የአየር ንብረት ብክለትን ለመከላከል ትልቅ ግብአት መሆኑንም አንስተዋል።

የድምጽ ብክለት የከተማዋ ተጨማሪ ችግር እየሆነ መምጣቱን አንስተው ችግሩ ከተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት  የሚመነጭ  መሆኑን አስረድተዋል።

የብክለት ችግሮቹን ከመሰረቱ ለመፍታት የተጀመሩ ጥረቶችን ለማጠናከር ግንዛቤን ማሳደግ እና የተቀመጡ ህጎችና መመሪያዎችን መተግበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ድዳ ድሪባ በበኩላቸው ንቅናቄው የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ጽዱና የበለጸገች አገር ለትውልድ የማስተላለፍ አላማ መያዙን ገልጸዋል።

የአካባቢ ብክለት በአካባቢ እና በሰው ልጅ ላይ ወቅታዊና ዘላቂ ችግር እንደሚያስከትል ገልጸው አሁን የተጀመረው ንቅናቄ ቋሚ አሰራር ሆኖ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም