የሽግግር  ፍትህ ፖሊሲ እና የፌዴራል አስተዳደር ሥነ ስርአት አዋጅ የዜጎች ሰብዓዊና ፍትሕ የማግኘት መብቶች እንዲከበሩ የሚያስችሉ ናቸው- አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

211

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 11/2016 (ኢዜአ)፦ የሽግግር  ፍትህ ፖሊሲ እና የፌዴራል አስተዳደር ሥነ ስርአት አዋጅ የዜጎችን ሰብዓዊና ፍትሕ የማግኘት መብት የሚያስከብሩ መሆናቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ።

በፌደራል አስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅ እና በሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ትግበራ ላይ ያተኮረ ውይይት መድረክ ተካሂዷል።

የሕዝብ ተወካየች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የዴሞክራሲ ተቋማት የስራ ሃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በውውይቱ ተሳትፈዋል።

አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ በዚህ ወቅት እንዳሉት በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አግባብ ባለው፣ በተቀናጀና አሳታፊ በሆነ መልኩ መፍትሄ ሳይሰጣቸው ቆይተዋል።

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሽግግር እና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሽግግር ፍትህ ሂደት መተግበር "ጠቃሚ ብቻ ሳይሆን እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ሀገራዊ አውዱ ያመላክታል" ብለዋል።

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መርሆችና ድንጋጌዎችን ያከበረ፣ የሀገሪቱን ፖለቲካና ማህበራዊ ዐውዶችን ባገናዘበ መልኩ መዘጋጀቱን አንስተዋል።

ፖሊሲው በገለልተኛ ባለሙያዎች ቡድን የተዘጋጀ፣ በባለድርሻ አካላትና ምሁራን ውይይት ተደርጎበት የጸደቀ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የነበሩ ቁስሎችን ሊያሽር፣ ቁርሾዎችን ሊያስቀር የሚያስችል የመፍትሔ ሀሳቦችን ይዞ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

መንግስት የዜጎችን ፍትህ የማግኘት መብት እንዲሁም የህግ የበላይነት እንደረጋገጥና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የሚያስችል የፌዴራል አስተዳድር ሥነ ስርዓት አዋጅ ተግባራዊ ማድረጉንም ተናግረዋል።

ሁለቱ የሕግ ማዕቀፎች የዜጎች ሰብዓዊ መብት እና ፍትህ የማግኘት መብት እንዲረጋገጥ ካመቻቸው ጉልህ ፋይዳ አኳያ ፍትህ ሚኒስቴርን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት ለተፈጻሚነቱ እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በበኩላቸው ዘመናዊ የመንግስት ስርዓት ከተጀመረ ረጅም ጊዜ ቢሆነውም የህግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ የተለያዩ ጉድለቶችና የዘፈቀደ ውሳኔዎች ይስተዋሉ ነበር ብለዋል።

በዚህም የመልካም አስተዳደር ችግር መስተዋሉን ገልጸው፤ እንደዚህ አይነት የህግ ማዕቀፎች ለብዙ ችግሮች መፍትሄ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

የህግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት ወሳኝ እርምጃ ቢሆንም ለተግበራዊነታቸው ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ በጥንቃቄና አሳታፊነቱን ተጠበቆ የተዘጋጀ፣ የላቀ ሀገራዊ ጠቀሜታ ያለው ፖሊሲ በመሆኑ  ለትግበራው የባለድርሻ አካላትን ትብብርና ክትትል እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

በዚህም በቀጣይ  የማስፈጸሚያ የሕግ ማዕቀፍ በማውጣት የሽግግፍ ፍትሕ ፖሊሲውን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም