የተሳታፊ ልየታ በተከናወነባቸው አካባቢዎች የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረኮችን ለመጀመር የሚያስችሉ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል-- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

320

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 11/2016 (ኢዜአ)፦ ለአገራዊ ምክክሩ የተሳታፊ ልየታ በተከናወነባቸው አካባቢዎች የአጀንዳ ማሰባሰቢያ ህዝባዊ መድረኮች ለመጀመር የሚያስችሉ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንደ ሀገር በሚስተዋሉ ችግሮች ላይ በመወያየት በዘላቂነት ለመፍታት፣ ብሔራዊ መግባባትና ሀገራዊ አንድነት ለመፍጠር በአዋጅ የተቋቋመ ገለልተኛ ተቋም ነው፡፡

ኮሚሽኑ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 1265/2014 ፀድቆ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ከሚሽኑ ኃላፊነቱን ተረክቦ ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ለምክክሩ ስኬት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ሲያሰባስብ ቆይቷል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት ለምክክሩ ውጤታማነት አስፈላጊ በሆኑ የተሳታፊ ልየታ መድረኮች መካሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡ 

በዚህም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና የህዝብ አደረጃጀቶች ጋር ሰፊ የውይይት መድረኮች በማዘጋጀት ተጨባጭ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል፡፡

በተሳታፊ ልየታው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ የዳያስፖራና የተለያዩ ትምህርት ተቋማት፣ በዕድሜና ጾታ ጭምር ተካተዋል ብለዋል።

የተሳታፊ ልየታ ባልተከናወነባቸው አካባቢዎች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ስራዎችን ለማጠናቀቅ እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ኮሚሽኑ ምክክር የሚደረግባቸው የአጀንዳ ሀሳቦችን ከጥናቶች፣ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ከህዝባዊ መድረኮች የማሰባሰብ ስልጣን እንደተሰጠው ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የተሳታፊ ልየታ በተደረገባቸው ክልሎች የአጀንዳ ሀሳብ ለማሰባሰብ የሚያስችሉ ህዝባዊ መድረኮችን ለመጀመር የሚያስችሉ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን አብራርተዋል፡፡

ምክክር ኮሚሽኑ በሀገሪቱ ከሚገኙ ከአንድ ሺህ 300 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚሳተፉ ተሳታፊዎች ጋር የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረኮችን ያዘጋጃል ብለዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም