ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ያህል ገቢ መሰብሰብ የሚያስችል ዘመናዊ አሰራርን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል-የፌዴራል ሱፐርቪዥን ቡድን

100

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 11/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያመነጨ ያለውን ገቢ በአግባቡ መሰብሰብ የሚያስችል ዘመናዊ አሰራርን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የፌዴራል ሱፐርቪዥን ቡድን አስታወቀ።

ቡድኑ የገቢዎች ሚኒስቴርና ጉምሩክ ኮሚሽን አጠቃላይ የስራ አፈፃፀም ግምገማና የተቋማቱ አሰራር ላይ ምልከታ አድርጓል።

በዚሁ ጊዜ ከተለያየ የፌዴራል ተቋማት የተወጣጡ የሱፐርቪዥን ቡድኑ አባላት ባለፋት ዓመታት የገቢ አሰባሰቡ ላይ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።

ገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ አሰባሰብ ስርዓቱን በቴክኖሎጂ ለመደገፍና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እያደረገ ያለውን ጥረትም አድንቀዋል።

ይሁንና ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ያህል ገቢ ከመሰብሰብ አኳያ ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን የቡድኑ አባላት አንስተዋል።

በተለይም የታክስ አሰባሰብ ስርዓቱን በቴክኖሎጂ የመደገፍ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውና አዳዲስ ግብር ከፋዮችን ወደ ሲስተም ማስገባት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በታማኝነት የሚከፍሉበትን ሁኔታ ማሳደግ፣ የታክስ ስርዓትን ማስፋት እንዲሁም ዘመናዊ ታክስ አስተዳደርና አሰባሰብ ስርዓትን ማጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል።

የገቢዎች ሚኒስትሯ አይናለም ንጉሴ የታክስ አሰባሰብ ስርዓቱ ላይ በተደረጉ የማሻሻያ ስራዎች የሚሰበሰበው ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል።

የኮንትሮባንድ ንግድ መከላከል ላይ መሻሻሎች መኖራቸውን ገልፀው፣ ህብረተሰቡ ወደ ህገ-ወጥ ንግድ እንዳይገባና የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን እንዳይጠቀም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በትኩረት እየሰራን እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ መሰብሰብ ላይ የተለያዩ ተግዳሮቶች መኖራቸውን አንስተው፤ ይህን ማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ አሰራሮችን በመዘርጋት ገቢውን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቀበታ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የዕድገት ፍላጎት ማሟላት የሚያስችሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በተሰሩ ስራዎች ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

ህገ-ወጥ የኮንትሮባንድ ንግድንና የጥቅም ትስስርን ማስቀረት የሚያስችሉ ግልፅ የአሰራር ስርዓቶች መዘርጋታቸውንም አመልክተዋል።

የጉምሩክ ኮሚሽን ለደንበኞቹ የ24 ሰዓት የኦንላይን አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አንስተው፤ አሰራሩን ይበልጥ ማሻሻልና ማዘመን ላይ በትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

May be an image of 7 people and people studying

All reactions:

1212

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም