አካባቢን ለኑሮና ለስራ ምቹ ለማድረግ ከደረቅ ቆሻሻና ፕላስቲክ ብክለት የመከላከል ንቅናቄ ይካሄዳል

ሐረር/ድሬዳዋ ፤ሚያዝያ 11/2016 (ኢዜአ)፦ አካባቢን ለኑሮና ለስራ ምቹ ለማድረግ ከደረቅ ቆሻሻና ፕላስቲክ ብክለት የመከላከል ንቅናቄ እንደሚያካሄድ የሐረሪ ክልል አካባቢ ጥበቃ እና የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣናት አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከሰሞኑ ከተሞቻችን እና አካባቢያችንን ጽዱ ለማድረግ እንተባበር ባሉት መልዕክታቸው እንደገለጹት፤ የፕላስቲክ እና የቆሻሻ ብክለት ሥነ ምህዳራችንን እና ጤናችንን አደጋ ላይ ይጥላል። 

''በሃላፊነት ስሜት ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ እና ዘላቂ አማራጮችን በመምረጥ ተፈጥሮን ለትውልድ ማቆየት እንችላለን'' ማለታቸው ይታወሳል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሐረሪ ክልላዊ መንግስት እና ድሬዳዋ አስተዳደር ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሃላፊዎች ችግሩን ለመግታት በትኩረት እንደሚንቀሳቀሱ አረጋግጠዋል።

በሐረሪ ክልል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ሃላፊ አቶ ሰሚር በክሪ እንደተናገሩት፤ ባለስልጣኑ በአካባቢ ብክለት፣ ቁጥጥርና ህግን ከማስፈፀም አኳያ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

አካባቢው ስነ ምህዳርና ተፈጥሯዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን የማጎልበት ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን በማከል።

በተለይ በክልሉ ከተማና ገጠር አካባቢዎች በከባቢ አየር፣ ውሃ፣ በአፈርና በድምፅ ብክለት ደረጃዎች ላይ የተቀናጀ የክትትልና ቁጥጥር ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በሐረር ከተማም ከተቋማትና ከሌሎች የሚወጡ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ጋር በተያያዘ ውስንነት እንደሚታይ የተናገሩት አቶ ሰሚር፤ ችግሩን ለመፍታት በተቀናጀ መልኩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በተለይም ደረቅ ቆሻሻን ከምንጩ ጀምሮ የማስወገድ ሂደቱ ስርዓቱን ጠብቆ እንዲከናወን እየተከታተለና በትክክል በማይፈጽሙት ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑንም ገልጸዋል።

እንደ አቶ ሰሚር ገለጻ፤ በተለይ ከአካባቢ ብክለት ጋር በተያያዘ በደረቅ ቆሻሻና ፍሳሽ  አወጋገድ ጋር ተግባራዊ ያላደረጉ ሁለት ተቋማትን በህግ አግባብነት የመጠየቅ ስራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።

በክልሉ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ እስከ መስከረም ድረስ ተግባራዊ የሚሆን የአካባቢ ጥበቃ ንቅናቄ እንደሚካሄድም ገልጸዋል። 

“ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ” በሚል መሪ ሃሳብ የሚከናወነው ይኸው ንቅናቄ የአካባቢ ጥበቃ ውጤታማነትን ለማሳደግ፣ የወጡ ሕጎችና ደንቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ፣ በዘርፉ የባለድርሻ አካላትንና የማኅበረሰቡን ሚና ለማጠናከር ያለመ መሆኑን አቶ ሰሚር ተናግረዋል። 


 

በተመሳሳይ የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱ መሐመድ በበኩላቸው፤ አካባቢን ውብና ፅዱ የስራና የመኖሪያ ስፍራ ለማድረግ የተጀመረውን አገር አቀፍ ዘመቻ ከግብ ለማድረስ በአስተዳደሩ የተቀናጀ ርብርብ እንደሚደረግ  ገልጸዋል።

አቶ አብዱ እንደሚናገሩት፤ አሁን የምንኖርባት አካባቢ ያለፈው ትውልድ ያወረሰን ብቻ ሳይሆን ከመጪው ትውልድ የተበደርን መሆኑን በመገንዘብ አካባቢን መንከባከብ ያስፈልጋል። 

ደረቅ ቆሻሻ በተለይም የፕላስቲክ ውጤቶች በመቅበርም ሆነ በማቃጠል አካባቢን ጽዱ ማድረግ እንደማይቻል የገለጹት አቶ አብዱ፤ ፕላስቲኮቹን በጥንቃቄ በመሰብሰብና በመፍጨት ሌሎች ቁሶችን በማምረት እንደሆነ ተናግረዋል።

በዚህም በድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ብክለትን ለመከላከልና የተፈጥሮ ሀብትን ለመጠበቅ የሚያግዝ የስድስት ወራት ዘመቻ መካሄድ መጀመሩን ገልጸዋል።

እስከ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በሚካሄደው በዚሁ ዘመቻ የሚያዝያ በሙሉ የፕላስቲክ ብክለትን በመከላከልና የፕላስቲክ አጠቃቀምን በማዘመን የስነ ምህዳርን ለመጠበቅ የሚያግዙ ህዝባዊ ንቅናቄዎች እንደሚካሄዱ አመልክተዋል።

ዘመቻው በተለይ በትምህርት ቤቶች የአካባቢ ጥበቃ ክበቦችንና ሚዲያን በመጠቀም እና በየደረጃው የሚገኘውን ህብረተሰብ ግንዛቤ በማስፋት ድሬዳዋ ለስራና ለኑሮ የምትመች ፅዱና ውብ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማሳካት እንደሚሰራ ነው የተናገሩት ።

በተጨማሪም ከከፍተኛ አመራሩ እስከ ህፃናት ተማሪዎች ድረስ የሚሳተፉበት የፕላስቲክ ኮዳዎችን የመሰብሰብ ና ፕላስቲኮችን ወደ ሌላ ምርቶች ለሚለወጡ ድርጅቶች የማስረከብ ስራ ይካሄዳል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም