ወጣቶች ሰላማቸውን በማስጠበቅ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የጀመሩትን ጥረት ማጠናከር አለባቸው - አቶ እንዳሻው ጣሰው

217

ወልቂጤ ፤ ሚያዝያ 11/ 2016(ኢዜአ)፦ወጣቶች የአካባቢያቸውን ሰላም በማስጠበቅ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የጀመሩትን ጥረት ማጠናከር እንዳለባቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ከጉራጌ ዞን የተለያዩ መዋቅሮች ከተወጣጡ ወጣቶች ጋር በወጣቶች የልማትና የመልካም አስተዳደር ተሳትፎና ተጠቃሚነት ላይ እየተወያዩ ነው።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት የክልሉ ወጣቶች የአካባቢያቸውን ሰላም በማስጠበቅ የልማትና መልካም አስተዳደር ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የጀመሯቸውን አበረታች ሥራዎች ማጠናከር አለባቸው።

ሰላም ለሁሉም መሠረት በመሆኑ ሰላማቸውን በቅንጅት ከማጠናከር ባለፈ በአካባቢያቸው የልማት ሥራዎች ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። 

ወጣቱ ትውልድ በመደመር ዕሳቤ ለውይይትና ለውስጥ ሰላሙ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስና ገዥ ትርክቶችን አጉልቶ ማውጣት እንዳለበትም ተናግረዋል።

አቶ እንዳሻው እንዳሉት ወጣቱ አዳዲስ እሳቤዎችን እያፈለቀና ባለው ላይ እየጨመረ የብልጽግና ጉዞን ለማፍጠን የሚደረገውን ጥረት ማገዝ አለበት።

በተለይ የሚያግባቡ እና የሚያስተሳስሩ ጉዳዮች አጉልቶ በማውጣትና የወል ትርክቶችን በማጠናከር የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ለማፋጠን መረባረብ ይኖርበታል።

ልማትን ለማጠናከር ዘላቂ ሰላምና የህዝቦች አንድነት ወሳኝ መሆኑን የገለጹት አቶ እንደሻው፣ በክልሉ ሁለንተናዊ ልማትን ለማፋጠን እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ወጣቶች የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም