ኮሚሽኑ በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ሀላፊነቱን እየተወጣ ነው---ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

215

ሻሸመኔ፤ ሚያዚያ 11/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ሀላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ። 

በኦሮሚያ ክልል በዞን፣ በወረዳና በከተማ አስተዳደር ደረጃ በምክክር ሂደቱ የሚሳተፉ የህብረተሰብ ተወካዮች ልየታ የማጠቃለያ መድረክ በሻሸመኔ ከተማ እየተካሄደ ነው። 

በመርሀ ግብሩ ላይ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ እና ምክትል ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ሒሩት ገብረስላሴ ተገኝተዋል።

ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን በመድረኩ እንደገለጹት ኮሚሽኑ እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር የተጣለበትን ሀላፊነት በአግባቡ ለመወጣት እየሰራ ነው።

የተጣለበትን ተልዕኮ ለመወጣት ገለልተኛ ተቋማትና ተባባሪ አካላትን ጭምር በማሳተፍ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ገልጸዋል።

በእዚህም ኮሚሽኑ የምክክር አጀንዳዎችን ከህብረተሰቡ ጋር የመቅረፅ፣ አጀንዳዎቹ ምክክር እንዲደረግባቸው የማመቻቸት እና ምክክሮችና ውይይቶችን የማሳለጥ ሃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ነው ፕሮፌሰር መስፍን ያስታወቁት

በኦሮሚያ ክልል የተሳታፊ ልየታ ሂደቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ የክልሉ መንግስት፣ የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር፣ ተባባሪ አካላትና ተሳታፊዎች ላደረጉት አስተዋጾም በኮሚሽኑ ሥም ምስጋና አቅርበዋል

በሻሸመኔ ከተማ እየተካሄደ ባለው የማጠቃለያ የማህበረሰብ ተወካዮች ልየታ መድረክ ከምስራቅ ቦረና ዞን የነገሌ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ከዋጭሌ፣ ዳሳ፣ አሬሮ፣ መደወላቡ፣ ጉሮዶላ እና ሊበን ወረዳዎች የተውጣጡ 500 የሚጠጉ የህብረተሰብ ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በመድረኩ የሀገራዊ ምክክር ምንነትና አስፈላጊነት እንዲሁም የአመራረጥ ሂደቱን በማስመልከት ለተሳታፊዎች ገለጻ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን ወደስራ ከገባ ጀምሮ በክልሎችና በከተማ መስተዳደሮች በርካታ የቅድመ ዝግጅት እና የተሳታፊ ልየታ ሥራዎችን አከናውኗል።

በቀጣይም ኮሚሽኑ የተሳታፊዎች ልየታ ባልተከናወነባቸው ክልሎች ልየታ በማድረግ አጀንዳዎችን በህዝባዊ ውይይቶች በማሰባሰብ ምክክሮች እንዲካሄዱ ያድርጋል።

በእዚህም አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያግዙ የሀገር ሽማግሌዎችንና በማህበሩሰቡ መካከል ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑትን የመለየትና ተቀራርቦ የመወያየት ስራዎችን እንደሚያከናወኑ ታውቋል። 

በምክክር ሂደቱ ውጤታማና በሃገሪቱ የተሻለ የሰላምና የፖለቲካ መደላድል እንዲፈጠር ሁሉም የበኩሉን አስተዋጾ ማበርከት እንዳለበት ኮሚሽኑ  በተለያዩ ጊዜያት ጥሪ ማቅረቡም የሚታወስ ነው።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም