ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ እና ማምረቻ ኢንዱስትሪ ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ አስቀምጡ

237

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 11/ 2016(ኢዜአ)፦የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ እና ማምረቻ ኢንዱስትሪ ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ አስቀምጡ።

የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ከተመሰረተ በርካታ ዓመታትን ያሳለፈው የመከላከያ ኢንዱስትሪ ዘመኑ ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ ለማድረስ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልፀው፣ የፋብሪካው ግንባታ ለሀገርና ለተቋሙ የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ኢንዱስትሪው በአዲስ መልኩ ከተደራጀ በኋላ በተሰሩት ስራዎች ከኪሳራ ወደ ትርፋማነት መሸጋገሩን የገለፁት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ የኮርፖሬሽኑ አመራርና አባላቶች ለነበራቸው ቁርጠኝነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ተቋሙ የራሱን ገቢ በማመንጨት ለሰራዊቱ መሰረታዊ ጥቅም ለማሟላት አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ የሰራዊቱን የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለማድረግና ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ በኢንዱስትሪ በግብርና በማዕድንና በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር ለመስራት የተቀመጠው አቅጣጫ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ሀይለማርያም የመከላከያ የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ እና ማምረቻ ኢንዱስትሪ ከሽርሽር ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር በመሆን የሚገነባው መሆኑን ተናግረዋል።

ኢንዱስትሪው በሰላሳ ሄክታር  መሬት ላይ የሚያርፍና በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

አለም አቀፍ ስታንዳርዳቸውን ያሟሉ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ከመገጣጠምና ከማምረት ባለፈ በቀጣይ ፕሮጀክቱን የማስፋፋት ዕቅድ እንዳላቸው የገለፁት ዳይሬክተሩ ለፕሮጀክቱ ስኬት ያልተቋረጠ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

በዝግጅቱ ላይ የመከላከያ ሚንስቴር ዲኤታ አቶ ቶማስ ቶት የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አቶ አለማየሁ አሰፋ ወታደራዊ አታሼዎች እንዲሁም  ከፍተኛ የሰራዊቱ አመራሮች መገኘታቸውን የመከላከያ ሠራዊት መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም