በሸገር ከተማ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ115 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል

93

አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 11/2016 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ115 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩን የከተማው ስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች  በሸገር ከተማ ገላን ጉዳ ክፍለ ከተማ በስራ ዕድል የተፈጠረላቸውን ዜጎች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

በዚህም በከተማው ስራአጥ ዜጎች በማህበር ተደራጅተው የስራ ዕድል ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኙ ተመልክተዋል።

የሸገር ከተማ የስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሃይሉ ደራርሳ፤ የሸገር ከተማ አስተዳደር ለስራ አጥ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ላይ ይገኛል ብለዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ115 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አብራርተዋል።

በ7 ሺህ 265 ማህበራት የተደራጁ ወጣቶች የስራ ዕድሉ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ለእነዚህ ዜጎች ከስልጠና ጀምሮ የመስሪያ ቦታ መመቻቸቱንም ተናግረዋል።


 

የስራ እድል የተፈጠረባቸው መስኮችም የማኑፋክቸሪንግ፣ የግንባታ፣ የእንሳሳት እርባታ፣ የወተት ላሞች፣ የዶሮ እርባታና የንግድ ዘርፍ ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የገላን ጉዳ ክፍለ ከተማ ስራ ዕድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍቅሩ ሃይሉ በበኩላቸው በክፍለ ከተማው በተለያዩ ዘርፎች ከ9 ሺህ 700 በላይ የሚሆኑ ዜጎች  የስራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ጠቁመዋል።

በክፍለ ከተማ የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች እንዳሉትም ለበርካታ ጊዜያት ያለ ስራ መቆየታቸውን ገለጸው፤ አሁን በስራ በመሰማራታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

እየሰሩ በሚገኙበት የወተት ላሞች፣ ስንጋ ማደለብ እና የዶሮ እርባታ ስራ ውጤታማ ለመሆን በመስራት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የሸገር ከተማ አስተዳደር 12 ክፍለ ከተሞች እና 36 ወረዳዎች አሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም