የመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና ችግሮች እንዲፈቱ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር ትሰራለች- ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

185

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 11/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና ችግሮች እንዲፈቱ ከወዳጅ አገራትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እንደምትሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።

በሰላም ዕጦት ውስጥ ያሉ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ሰላምና መረጋጋት እንዲረጋገጥም አበክራ እንደምትሰራም ገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟንና ፍላጎቷን መሰረት ያደረገ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲን ታራምዳለች።

'የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አልፋና ኦሜጋ ብሔራዊ ጥቅም ነው' ያሉት አምባሳደሩ፣ ዲፕሎማሲው ከሀገር ሰላም፣ ልማትና ደህንነት አኳያ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ነው ያነሱት።

በዚህም በተለዋዋጩ ዓለም ውስጥ ኢትዮጵያ የምትወስዳቸው አቋሞች ከራሷ ብሔራዊ ጥቅም አኳያ መዝና እንደሆነ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር ካላት መልክዓ ምድራዊና የህዝብ ለህዝብ ትስስር አኳያ የቀጣናው ቀውስና መረበሽ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ቀጥተኛ አንድምታ እንዳለው ተናግረዋል።

በዚህም የቀጣናው ችግሮች እንዲፈቱና ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሞች እንዲከበሩ ከአጋር አገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እንደምትሰራ ገልፀዋል።

በተመሳሳይ ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ለጎረቤት ሀገራት ቀዳሚ ትኩረት እንደምትሰጥ ገልፀው፣ በተለይም ጎረቤት አገራት ቀውስ ለኢትዮጵያ እንደሚተርፍ ተናግረዋል።

በዚህም በሰላም ዕጦት ለሚቸገሩ ጎረቤት አገራት ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር በታሪክ የነበራትን የሰላም ማስከበር ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

ከሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ባሻገርም ኢትዮጵያ በቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል የዲፕሎማሲ ስራዎችን ማከናወኗን ገልጸዋል።

የባሕር በርን ጨምሮ ፀጋዎችን አልምቶ በጋራ በመጠቀምና የመሰረተ ልማትና ንግድ ትስስር በማጎልበት የጋራ ዕድገትን ማረጋገጥና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም