በአማራ ክልል የፕላስቲክ  አወጋገድን በማዘመን ከብክለት ነፃ  የሆኑ ከተሞችን ለመገንባት ጥረት እየተደረገ ነው

ባህር ዳር ሚያዚያ 11 / 2016 (ኢዜአ)-  በአማራ ክልል የፕላስቲክና የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን በማዘመን ከብክለት ነፃ የሆኑ ከተሞችን ለመገንባት ጥረት እየተደረገ  መሆኑን የክልሉ የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ባስተላለፉት መልዕክት፤  የፕላስቲክ እና የቆሻሻ ብክለት ሥነ ምኅዳራችንን እና ጤናችንን አደጋ ላይ እንደሚጥል መግለጻቸው ይታወሳል። 

እርሳቸው "በኃላፊነት ስሜት ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ እና ዘላቂ አማራጮችን በመምረጥ ተፈጥሮን ለትውልድ ማቆየት እንችላለን" በማለት ከተሞችን እና አካባቢያን ጽዱ ለማድረግ የመተባበር አስፈላጊነትን አጽንኦት ሰጥተውታል።

የፕላስቲክ ቆሻሻ ለዓመታት ከምድር ላይ የማይጠፋ ለአካባቢ ብክለት ዋነኛ መንስኤ እየሆነ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ።

በተለይ ከተሞች ለዚህ ችግር ሰለባ ናቸው።  በገጠር አካባቢ ለግብርና ስራ ችግር ፈጣሪ እየሆነ መምጣቱና ፕላስቲክ የበሉ ላሞች እንደሚሞቱ  ይገለጻል። 

ይህን እንዴት እየተከላከሉ እንደሆኑ ኢዜአ የጠየቃቸው በአማራ ክልል የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክተር አቶ አወቀ ይቴ በሰጡት ምላሽ  "ከፕላስቲክና ከደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ጋር ተያይዞ ሊያጋጥም የሚችለውን ብክለት ለማስቀረት በትኩረት እየተሰራ ነው" ብለዋል። 

ለዚህም የፕላስቲክና የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን በማዘመን ከተቋማትና ከሌሎች አካላት ጋር አስተሳስሮ ለመምራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የተለያዩ ማህበራትን በባህር ዳር፣ ደሴ፣ ጎንደርና ሌሎች ትላልቅ ከተሞች በማቋቋም ፕላስቲክን ለይተው በማሰባሰብ የማስወገድ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

በዚህም በወር 30 እስከ 40 ቶን የወዳደቁ ፕላስቲኮች እንደሚሰበሰቡ አመልከተው፤ ከእነዚህም  የፕላስቲክ ወንበሮች፣ ለገመድና ሌሎች ምርቶችን በማምረት ጥቅም ላይ እንዲውል እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የቀረውንም በመጨፍለቅና በመፍጨት አዲስ አበባን ጨምሮ   ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሚጓጓዝበት ሁኔታ እንዳለም ጠቁመዋል።

የፕላስቲክ ምርቶች ቀደም ሲል በዘፈቀደ በየቦታው የሚጣልበት ሁኔታ እንደነበረ አስታውሰው፤ "አሁን ላይ የሚጣሉ የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን በመሰብሰብና በማስረከብ በርካታ ወጣቶች የገቢ ምንጭ እያደረጉት ይገኛሉ" ብለዋል።

ፕላስቲኮች በወንዞንች፣ በውሃ ማፋሰሻ ቦዮችና አካባቢ ስነ-ምህዳር ላይ ጉዳትና ብክለት እንዳያስከትሉ በአሰባሰብና አወጋገዱ ላይ ያተኮረ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም