የአካባቢ ብክለትን መከላከል የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል- ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሁመድ

ጅግጅጋ፤ ሚያዚያ 11/2016(ኢዜአ)፡- የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ፅዱና ለኑሮ የሚመች አካባቢ መፍጠር የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ሲሉ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሁመድ ገለጹ።

ርዕስ መስተዳድሩ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የሚተገበር የህዝብ ንቅናቄ ዛሬ በክልል ደረጃ አስጀምረዋል።

በርዕሰ መስተዳድሩ ጽህፈት ቤት በተጀመረው የንቅናቄ መድረክ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ እንደተናገሩት በክልሉ የአካባቢ ብክለት ችግር ለመፍታት

አንዱ የፕላስቲክ አጠቃቀምና አወጋገድን ማዘመን ያስፈልጋል።

በክልሉ እየተስፋፉ ያሉ ከተሞች ላይ በመመስረት አካባቢ ከብክለት ነፃ እንዲሆን ሴክተር መስሪያ ቤቶች በዕቅዳቸው ውስጥ በማካተት እንዲሰሩ ትኩረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።


 

በአርብቶ አደር አካባቢ የቤት እንስሳት በፕላስቲክ አወጋገድ ችግር ጉዳት ይደርስባቸዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የፕላስቲክ ምርቶችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋልና በዚህም የስራ እድል ለመፍጠር ሊሰራ እንደሚገባ አሳሰበዋል።

የንቅናቄ መድረኩ ህብረተሰቡ በጉዳዮ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ኖሮት የድርሻውን እንዲወጣ ለማነሳሳት መሆኑን አመልክተዋል።

የክልሉ የአካባቢ ጥበቃና ገጠር መሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ኢንጀነር ሙህየዲን አብዲ ፤ የአካባቢ ብክለት በአካባቢ ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን ተናግረዋል።

ችግሩን ለመፍታት የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማስፋት ትኩረት ተስጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በንቅናቄው መድረክ የተገኙት የፌደራል የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሴ ለማ በበኩላቸው፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው ንቅናቄ የአካባቢ ብክለት በሰው እና በእንስሳት ላይ ሊያደረስ የሚችለውን ጉዳት ለማስቀረት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የፕላስቲክ አጠቃቀም ገደብ ላይ ህግ በማዘጋጀት ለሚመለከተው አካል ማቅረቡንም ጠቅሰዋል።

"ብክለት ይብቃ! ውበት ይንቃ" በሚል መሪ ሀሳብ የተጀመረው ንቅናቄ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የሚተገበር ስራ እንደሚከናወን ተመልከቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም