ራይድ እና ቪዛ በኢትዮጵያ የትራንስፖርት ክፍያን ለማቀላጠፍ የሚያስችል ጥምረት መፍጠራቸውን አስታወቁ

100

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 11/2016 (ኢዜአ)፦ ራይድ ትራንስፖርት እና ታዋቂው ዓለም አቀፍ የዲጂታል ከፍያ ተቋም ቪዛ በኢትዮጵያ የትራንስፖርት ክፍያን ለማቀላጠፍ የሚያስችል ጥምረት መፍጠራቸውን አስታወቁ፡፡

ጥምረቱ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የውጭ አገር ዜጎች እና ዲያስፖራዎች የቪዛ ካርዳቸውን ብቻ በመጠቀም የትራንስፖርት ክፍያቸውን እንዲያከናውኑ የሚያስችል ነው፡፡

ይህም ጎብኚዎች አስተማማኝና ቀልጣፋ ትራንስፖርት በማግኘት በኢትዮጵያ አስደሳች ቆይታ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡

የሃይብሪድ ዲዛይንስ እና ራይድ መስራች ሳምራዊት ፍቅሩ፤ ጥምረቱ "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" እውን ለማድርግ እየተከናወነ ካለው ስራ ጋር የሚጣጣም መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቪዛ ዳይሬክተር ያሬድ እንዳለ በበኩላቸው፤ ቪዛ የተቀላጠፈ እና አስተማማኝ የዲጂታል ክፍያን ለሁሉም እና በሁሉም ቦታ ለማዳረስ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በመሆኑም ከራይድ ጋር የተጀመረው ጥምረት የኢትዮጵያን የጉዞ እና ቱሪዝም ዘርፍ ለማዘመን ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም