ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመዲናዋ የብክለት መከላከል ንቅናቄን አስጀመሩ

69

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 11/2016 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመዲናዋ የብክለት መከላከል ንቅናቄን በዛሬው ዕለት አስጀምረዋል።

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ በሚል መሪ ሃሳብ በከተማችን የብክለት መከላከል ንቅናቄ አስጀምረናል ብለዋል።

ተፈጥሮ ለአዲስ አበባ የለገሳትን ውበት ያመናመነውን አሰራር ለመቀየር እና የከተማውን ስርዓተ-ምህዳር ለማሻሻል የሚረዱ ሜጋ ፕሮጀክቶች በከፍተኛ ርብርብ፣ በልዩ የአመራር ትኩረት እና በአጠረ ጊዜ መፈጸማቸውን ገልጸዋል።


 

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፤ ከፍተኛ ለውጥ እያመጡ ካሉት ፕሮጀክቶች መካከል ዋነኞቹ ለሞቱት የከተማዋ ወንዞች ትንሳኤያቸውን፤ ለተበከሉት ደግሞ ህክምናን ያበሰረው የአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻ ልማት አንዱና መሰረታዊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በከፍተኛ ፍጥነት እየቀነሰ የነበረውን የከተማዋን የአረንጓዴ ሽፋን የታደገው እና ከነበረበት 2 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 15 በመቶ ያሳደገው የአረንጓዴ አሻራ ማኖር ኢኒሼቲቭ ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸዋል።

የተሰሩት ስራዎች አዲስ አበባን የቱሪስት መዳረሻና ዓለም አቀፍ የስበት ማዕከል ያደረጓት ቢሆንም፤ አሁንም ድረስ የድምጽ እና የፍሳሽ ብክለት እና አወጋገድ የከተማዋ ፈተናዎች ሆነው መቀጠላቸውን ተናግረዋል።

በሕግና በአሰራር ችግሩን ለመፍታት ከሚደረግ ጥረት ባሻገር፤ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት የሚቆይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በመስራት ለውጥ ለማምጣት ንቅናቄው በዛሬው ዕለት በይፋ መጀመሩን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም