ከኖርዌይ መለስ በአትክልትና ፍራፍሬ ሸበዲኖን እያለሙ ያሉ ጥንዶች

110

አዋሳ፣ሚያዝያ 11/2016 (ኢዜአ)፡ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ከኖርዌይ የተመለሱት ጥንዶች በሲዳማ ክልል በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ተሰማርተን ለሀገራዊ እድገት የድርሻችንን እየተወጣን ነው ይላሉ።

ጥንዶቹ ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት ለይታ በማልማት የዜጎቿን  ሕይወት ለመለወጥ ሰፊ ዕድል እንዳላት ይናገራሉ።

በአውሮፓዊቷ  ሀገር ኖርዌይ ኑሯቸውን ለ12 ዓመታት አድርገው የነበሩት ጥንዶች በአሁኑ ወቅት በሲዳማ ክልል ሸበዲኖ ወረዳ ሞሮቾ ሻንዶሎ ቀበሌ ሦስት ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ አትክልትና ፍራፍሬ እያለሙ ነው።


 

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ወደ ሥልጣን መምጣት እና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተጀመረው ልማት ወደ  ኢትዮጵያ ለመመለስ ምክንያት እንደሆናቸው ይናገራሉ።

አቶ አየለ ታዬ በኖርዌይ ቆይታቸው ሥራን ጨምሮ ለኑሮ የተመቹ በርካታ ዕድሎች ቢኖራቸውም፤ በሀገር ከመኖርና ከመስራት የተሻለ አማራጭ ባለመኖሩ ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱ ተናግረዋል።


 

የባለቤታቸው ትውልድ ቦታ በሆነው ሸበዲኖ ወረዳ ያለው የተፈጥሮ ሃብትና ለም መሬት ''ባለን የተፈጥሮ ጸጋ ላይ ተፈጥሮን በመንከባከብ በአጭር ጊዜ ልንለወጥ እንችላለን'' የሚል አስተሳሰብ እንዲፈጠርባቸው ማድረጉን ተናግረዋል።

''ያለን ሀብት በአግባቡ አልምቶ ለመጠቀም የሁሉም የተቀናጀ ጥረት ያስፈልጋል'' ያሉት አቶ አየለ፣ እንደ ሀገር ለተያዘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር  ስኬታማነት የድርሻቸውን ለማበርከት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የቤተሰብ ይዞታ በሆነው መሬት ላይ በዋናነት ከአቦካዶ በተጨማሪ ቡና፣ ፓፓያ፣ ግሽጣ፣ ማንጎን ጨምሮ የተለያዩ ፍራፍሬና አትክልቶችን ማልማታቸውን ነው የተናገሩት።

በመጀመሪያው ዙር ካለሙት 20 ኩንታል አቦካዶ፣ 500 ኩንታል ፓፓያ እና ሌሎች ምርቶችን ለሽያጭ ማቅረባቸውን የሚናገሩት  አልሚው፤ ዘንድሮ ከዚህ በላይ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል። 

"በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሥራቸው በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ አካባቢውን አረንጓዴን በማልበስ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ህልም ለማሳካትና ለሀገራዊ ዕድገት የሚጠበቅብንን እየተወጣን ነው" ብለዋል።

ወረዳው ለግብርና ሥራ ምቹ የሆነ የተፈጥሮ ሀብትና የአየር ጸባይ ያለው በመሆኑ ጠንክሮ መስራት ከተቻለ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል አቶ አየለ ተናግረዋል። 

የሲዳማ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በማሳቸው ተገኝተው የአቦካዶ ችግኝ ተከላ ማካሄዳቸው ብርታት እንደሆናቸው የገለጹት አቶ አየለ፣ ድጋፍና  ክትትሉ በአጭር ጊዜ የደሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት እንደሚያስችል እምነታቸውን ገልጸዋል።

ባለቤታቸው ወይዘሮ ራሔል ሰብስቤ በበኩላቸው በአካባቢው ታዋቂ  የነበሩት ሴት አያታቸው ጎበዝ አርሶ አደር እንደነበሩ ይገልጻሉ። 


 

ከባለቤታቸው አቶ አየለ ጋር ከኖርዌይ ከተመለሱ በኋላ በልጅነታቸው ለዕረፍት ይመጡበት የነበረው አካባቢ አረንጓዴነቱን ጠብቆ ማግኘታቸው ለተፈጥሮ ትኩረት እንዲሰጡ ያደረጋቸው መሆኑን አስረድተዋል።

አያታቸው "ለም መሬትና ውብ ሀገር እያለሽ ለምን ከሀገርሽ ትወጪያለሽ?" እያሉ በሀገራቸው እንዲኖሩ ይመክሯቸው እንደነበር እና በወጣትነት ዘመን ስደትን መምረጣቸውን እንዳልወደዱላቸው  ያስታውሳሉ።

በአሁኑ ወቅት ወደ ትውልድ ሥፍራቸው ሲመለሱ አያታቸውን በህይወት ባያገኞቸውም፤ በአያታቸው መሬት ላይ የግብርና ልማት በመጀመራቸው ደስተኛ መሆናቸውንና በመንግስት በኩልም ለልማቱ የተለያየ እገዛ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ አየለ እንዳሉት "ፓራዳይስ ፍሩት ጋርደን" በሚል የጀመሩትን የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሥራ ወደፊት አስፍተው ለመስራትና በምርቱ ላይ እሴት በመጨመር የኮስሞቲክስ ኢንዱስትሪ የማቋቋም እቅድ አላቸው።

በአውሮፓ በነበራቸው ቆይታ የሰዓት አጠቃቀምና የሥራ ባህል ላይ ጥሩ ተሞክሮ ማግኘታቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ ራሔል፣ ''በተፈጥሮ ጸጋ ግን ኢትዮጵያን የሚያክል ሀገር አላየሁም'' በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ይሄንን የተፈጥሮ ጸጋ ማልማት ከዘርፈ ብዙ ችግሮቻችን መውጫ መንገድ በመሆኑ በተሰማሩበት መስክ የድርሻቸውን ለመወጣት ከትዳር አጋራቸው ጋር ኑሯችንን በማሳ ውስጥ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የሸበዲኖ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኤልያስ አየለ በበኩላቸው የጥንዶቹ ማሳ የሚገኝበት አካባቢ በወረዳው 67ኛ የአቦካዶ ክላስተር ሆኖ ዘንድሮ የችግኝ ተከላ እንደተከናወነበት ገልጸዋል።

ጥንዶቹን ጨምሮ በ16 የአርሶ አደሮች ኩታ ገጠም ማሳ ላይ 566 የአቦካዶ ችግኞችን በመትከል የፍራፍሬ ልማቱን ለማስፋትና አርሶ አደሮቹን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።               

የሲዳማ ክልል የ2016 በጀት ዓመት የቡናና ፍራፍሬ ችግኝ ተከላ በሸበዲኖ ወረዳ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት እንደተጀመረ መዘገቡ ይታወሳል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም