ኮሚሽኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሀብት ማሳወቅና ምዝገባ እንዲሁም የሙስና መረጃ ትንተናና ጥቆማ መቀበል ረገድ የተሻለ ስራ መስራቱን ገለጸ

89

አዳማ ፤ ሚያዝያ 11/2016(ኢዜአ)፦ የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሀብት ማሳወቅና ምዝገባ እንዲሁም የሙስና መረጃ ትንተናና ጥቆማ መቀበል ረገድ የተሻለ ስራ መስራቱን ገለጸ።

የሁሉም ክልሎች የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽነሮች የተሳተፉበት በሙስና ተጋላጭነት ዙሪያ የምክክር መድረክ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በኮሚሽኑ የስነ-ምግባር ግንባታ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት በሀብት ማሳወቅና ምዝገባ እንዲሁም የሙስና መረጃ ትንተናና ጥቆማ መቀበል ላይ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተሻለ ሥራ ተሰርቷል።

በተለይም በአስቸኳይ ሙስና መከላከል ስራና የሙስና ስጋት ተጋላጭነት ጥናት በትኩረት መከናወኑን ጠቅሰው፣ በዚህም በርካታ የህዝብና የመንግስት ሀብትን ከምዝበራ መታደግ ተችሏል ብለዋል።

በተጨማሪም የክልሎችን የስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽነሮች አቅም የመገንባት፣ ተቋማዊ የሙስና መከላከል አቅም ግንባታና የሙስና መከላከል ሪፎርም ላይ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውንም አስታውቀዋል።

በስነ-ምግባር ግንባታና በሙስና መከላከል ስራ የተሻለ ውጤት መገኘቱን ገልጸው፤ መድረኩ የክልሎች የፀረ ሙስና ኮሚሽን ልምድ የሚለዋወጡበትና የሚማማሩበት መሆኑንም አመልክተዋል።


 

በኮሚሽኑ የሙስና መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አቶ እሸቴ አስፋው በበኩላቸው ኮሚሽኑ በ25 ዘርፎች ላይ የሙስና ተጋላጭነት ጥናት ለማድረግ አቅዶ በ19ኙ ላይ ማከናወኑን አስታውቀዋል።

ቀሪዎቹ  ዘርፎች ላይ የሙስና ተጋላጭነት ጥናት እየተካሄደ  መሆኑን በማከል።

የሙስና ትግሉ የታለመለትን ግብ እንዲያሳካ መብቱን በገንዘብ የማይገዛና ሙስናን መሸከም የማይችል ማህበረሰብ መገንባት ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

የሙስና መከላከልና የዘርፉን ህግ ማስፈፀም ላይ የፖለቲካ አመራሩና ኮሚሽኑ ተቀናጅተው መስራት እንደሚገባቸውም ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የአሰራር ስርዓት ማዘመንና ለህዝብ የሚሰጠውን አገልግሎት በቴክኖሎጂ ማስደገፍ ለፀረ ሙስና ትግል ስኬት ቁልፍ አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።

የሙስናና ብልሹ አሰራር መንስዔን በጥናት በመለየት አስቸኳይና መደበኛ የሙስና መከላከል ስራዎችን ማጠናከር ከሁላችንም የሚጠበቅ ቀዳሚ ተግባር ነው ሲሉም አሳስበዋል።

በየደረጃው ያሉ የፌዴራልና የክልል የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽኖች የአሰራር ስርዓታቸውን በቴክኖሎጂ አስደግፈው መምራት እንደሚገባቸው በማጽናት።

በግዥ፣ በግንባታ፣ በአገልግሎት አሰጣጥና በፍትህና በመሬት ላይ የሚፈፀም ሙስናን ለመከላከል የጋራ ዕቅድ ሊኖረን ይገባል ነው ያሉት።

የመሬት ሀብቱን ወደ ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ካዳስተር ማስገባትና በቴክኖሎጂ በመምራት በዘርፉ የሚፈፀም ሙስናና ምዝበራ መግታት እንደሚገባም ምክትል ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም