በኢሉባቦር ዞን የሻይ ተክልን ለማስፋፋት ከ206 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል --- ጽህፈትቤቱ

92

መቱ፤ ሚያዝያ 11/2016 (ኢዜአ)፦በኢሉባቦር ዞን የሻይ ልማትን ወደ 13ቱም ወረዳዎች ለማስፋፋት ከ206 ማሊዮን በላይ ችግኞች  ለተከላ መዘጋጀታቸውን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በሻይ ልማት የተሰማሩ የአሌ ወረዳ አርሶ አደሮችም ልማቱን በማስፋፋት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን ለማሳደግ አቅደናል ብለዋል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ቻላቸው አዱኛ ለኢዜአ እንደተናገሩት በዞኑ እስካሁን የሻይ ልማት የሚካሄደው በአምስት ወረዳዎች በሚገኙ አርሶ አደሮች ነው።


 

በአርሶ አደሮቹ  በመልማት ላይ የሚገኘውም 328  ሔክታር ብቻ መሆኑንም አመልክተዋል። 

ሆኖም  በዚህ ዓመት ለልማቱ በተሰጠው ትኩረት ልማቱን ወደ ስምንት  ወረዳዎች ለማስፋፋት በ13ቱም ወረዳዎች በኩታ ገጠም 12ሺህ ሔክታር  መለየቱን አስረድተዋል።

ልማቱን ለማስፋፋት ከችግኝ ዝግጅት ባሻገር በሁሉም ወረዳዎች በልማቱ የሚሰማሩ 32 ሺህ አርሶ አደሮች ለማሳተፍ ዝግጅት መደረጉን ኃላፊው ገልጸዋል።  

የሻይ ተክል የአፈር አሲዳማነትን የሚከላከልና ምርታማነቱ ከፍተኛ በመሆኑ የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ልማቱን ለማስፋፋት ትኩረት መሰጠቱን አቶ ቻላቸው ተናግረዋል።

በሻይ ልማት የተሰማሩ የአሌ ወረዳ አርሶ አደሮች ሥራውን በማስፋፋት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ዕቅድ መያዛቸውን አስታውቀዋል።

በአሌ ወረዳ የጉመሮ አቦ ቀበሌ ነዋሪ አቶ እንዳለ ብርሃኑ በአሁኑ ሰዓት በሰባት ሔክታር የሻይ ተክል እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በግብርና ባለሙያዎች ሙያዊ ድጋፍ ታግዘው ሥራውን መጀመራቸውን የገለጹት አርሶ አደሩ፣ ''ምርቱ በየወሩ ሁለት ጊዜ ስለሚለቀም ከሌላው የግብርና መስክ በይበልጥ ተጠቃሚ ያደርገኛል'' ብለዋል።

አቶ ከበደ ተረዳ የተባሉት አርሶ አደር ካላቸው ማሳ በሶስት ሔክታር ያህሉ ላይ የሻይ ተክልን ማልማት መጀመራቸውን ገልጸው፣ ይህም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያረጋግጥላቸው ተናግረዋል።

የጉመሮ ሻይ ልማት ድርጅት በአካባቢያቸው የሚገኝ በመሆኑ ልምድ የሚቀስሙበትና ምርታቸውንም የሚያቀርቡበት በመሆኑ መልካም አጋጣሚ እንደሆናቸው ጠቅሰዋል።

በቀጣይ ወደ ሻይ ልማት ግብርና ለመግባት አቅደው የማሳ ዝግጅት ሥራ በማከናወን ላይ እንደሚገኙ የመቱ ወረዳ ነዋሪ አቶ ሺበሺ ለማ፣ሥራውን አስቀድመው ከጀመሩ አርሶ አደሮች ልምድ በመውሰድ ወደ ልማቱ ለመግባት ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም