በመቀሌ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎችን እያከፋፈልኩ ነው - አገልግሎቱ

90

መቀሌ፤ ሚያዝያ 11/2016 (ኢዜአ):-በመቀሌ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ስማርት የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎችን ለደንበኞቹ እያሰራጨ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የትግራይ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ገብረመድህን ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ስማርት ቆጣሪዎቹ ከአገልግሎት ሂሳብና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በፍጥነት በመጠቆም መፍትሄ ለማስገኘት ያስችላሉ።  

በመጀመሪያ ዙር ወደ ክልሉ ከገቡት አራት ሺህ ዘመናዊ ቆጣሪዎች ውስጥም ሁለት ሺህ ያህሉን ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ለሚጠቀሙ የአምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲገጠሙ መደረጉን ጠቁመዋል። 


 

ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ከሚጠቀሙና ስማርት ቆጣሪዎቹ ከተሰጣቸው ድርጅቶች መካከልም በማኑፋክችሪንግ፣ በሆቴል እና በመስኖ ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት እንደሚገኙበት ተናግረዋል። 

ዘመናዊ ቆጣሪዎቹ ከዚህ ቀደም የነበረውን አመቺ ያልሆነ አገልግሎት አሰጣጥ የተሻለ ለማድረግ እንደሚያስችሉ አቶ መስፍን ገልፀው፤ ''በካርድ የሚሰሩ ዘመናዊ የመኖርያ ቤት ቆጣሪዎችን ጥቅም ላይ ለማዋልም ክልሉ የአጭርና የመካከለኛ ጊዜ የአፈፃፀም እቅድ ይዞ እየተሰራበት ነው'' ብለዋል። 

ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ከሚጠቀሙ ድርጅቶች መካከል በመቀሌ የሚገኘው የኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉዓለም ወልደንጉስ በድርጅታቸው የተገጠመው ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ ከክፍያ ጋር በተያያዘ ይገጥም የነበረውን የኃይል መቋረጥ እንደሚያቃልል ተናግረዋል።  

ከዚህ በፊት ሲሰጥ የነበረው በሰው ኃይል የታገዘ የቆጣሪ ንባብና ብልሽትን የመለየት ሥራ ውጣ ውረድ የበዛበት በመሆኑ በኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥና ክፍያ አፈፃፀም ላይ ብዙ ችግር ይፈጥር እንደነበር የገለጹት ደግሞ በመቀሌ የሁዳ ዱቄት ማምረቻ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ ይርጋ ከበደ ናቸው። 

''በቅርቡ በድርጅታችን ውስጥ የተገጠመው ስማርት ቆጣሪ ያለ አንዳች መንገላታት ክፍያችንን በወቅቱ ለመፈፀም አስችሎናል'' ብለዋል አቶ ይርጋ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም