የሽግግር  ፍትህ ፖሊሲ በኢትዮጵያ  ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን የሚያስችል መፍትሄ ይዞ ተዘጋጅቷል- አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ 

123

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 11/2016(ኢዜአ)፦ የሽግግር  ፍትህ ፖሊሲ ለዘመናት ሲንከባለሉ ለመጡ ቁርሾች መፍትሄ በመስጠት ዘላቂ ሰላም ና መረጋጋት ማስፈን በሚያስችል አግባብ መዘጋጀቱን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ።

አፈ ጉባኤው ይህን የተናገሩት በፌደራል አስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅ እና በሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ላይ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ነው።

በኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አግባብ ባለው፣ ሁለንተናዊ፣ የተቀናጀና አሳታፊ በሆነ መልኩ መፍትሄ ሳይሰጣቸው መቆየታቸውን አንስተዋል።

በመሆኑም ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ እንዲቻል የሽግግር ፍትህ ሂደት መተግበር  "ጠቃሚ ብቻ ሳይሆን እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አገራዊ አውዱ ያመላክታል" ብለዋል።

ከዚህ አኳያ አሳታፊ፣ ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶችና መርሆችና ድንጋጌዎችን ያከበረ፣ የአገሪቱን ፖለቲካና ማህበራዊ አውዶችን መሰረት ያደረገ የሽግግር ፍትህ ሂደት መቀመርና በግልጽ የፖሊሲ ማዕቀፍ እንዲመራ ለማድረግ ፖሊሲው መዘጋጀቱን ገልጸዋል።


 

ፖሊሲው በጥናትና ምርምር ላይ የቆዩ ገለልተኛ የሙያተኞች ቡድን የተዘጋጀ ፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትና ምሁራን ውይይት አድርገውበት በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁን አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ መግባባትን ወደፊት ለማስቀጠል ቁስሎችን ሊፈውስ እና ቁርሾዎችን ሊያስቀር የሚያስችሉ የመፍትሔ ሀሳቦችን ይዞ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የዜጎችን የአሰተዳደር ፍትህን ለማረጋገጥ  ስራ ላይ የዋለው የአስተዳደር ስነ-ስርአት አዋጅ ላይ የሚነሱ ክፍተቶች ማረም ላይ በቀጣይ በትኩረት አንዲሰራ አሳስበዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የዴሞክራሲ ተቋማትና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም