በአፍሪካ ቀንድና በቀጣናዊ ደህንነት ላይ ያተኮረ ውይይት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

174

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 11/2016 (ኢዜአ)፦ በአፍሪካ ቀንድና ቀጣናዊ ደህንነት ላይ ያተኮረ ውይይት በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ያዘጋጀው ውይይት “ለውስብስብ ጉዳዮች አማራጭ መንገዶችን በመፈለግ፤ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ደህንነትን ማረጋገጥ” በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተካሔደ ያለው።

በውይይቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ የውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።


 

በቀጣናው የደህንነት ምህዳር ላይ እየታዩ ያሉ ለውጦችና አንድምታቸው፣ የውጭ ኃይሎች በቀጣናው ደህንነት ላይ ያላቸው ሚና ላይ ያተኮሩ የመነሻ ጽሑፎች ቀርበው ውይይቶች እንደሚካሔድባቸውም ተገልጿል።

ጠንካራና የተሳሰረ ቀጣና ግንባታ ለዘላቂ ሰላምና መልካም እድሎች ያለውን ሚና የተመለከቱም ጽሁፎች ቀርበው የፓናል ውይይቶች እንደሚደረግባቸውም ገልጸዋል።

በዛሬው እለት የሚካሔደው ውይይት የአፍሪካ ቀንድን አስመልክቶ እየተካሄዱ ያሉ ውይይቶች ቀጣይ አካል መሆኑ ተገልጿል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሐምሌ 2023 መሰል ውይይት በጅቡቲ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

የውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩት በውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ፣ በሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ጥናትና ምርምር በማከናወን አገራዊ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የምክከር መድረኮችን በማዘጋጀት ለፖሊሲ አማራጭ ምክረ ሀሳቦችን የሚያቀርብ ተቋም ነው።

በተጨማሪም ኢኒስቲትዩቱ ለዲፕሎማቶችና ለባለድርሻ አካላት ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም