በክልሉ የተጀመረው ከሳምንት እስከ ሳምንት ገበያ ዋጋ በማረጋጋት ተጠቃሚ አድርጎናል--ሸማቾች እና ነጋዴዎች

75

 ሆሳዕና፤ ሚያዚያ 11/2016 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከሳምንት እስከ ሳምንት በሚል የተጀመረው ገበያ የመሰረታዊ ፍጆታዎችን ዋጋ በማረጋጋት ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ሸማቾች እና ነጋዴዎች ገለጹ።

በክልሉ የቡታጅራ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ዙለይካ ሱልጣን ለኢዜአ እንደገለጹት፣ማህበረሰቡ የገበያ አማራጭ እንዲኖረው በተለይ ምርቱን ከአምራቹ በቀጥታ እንዲያገኝ መደረጉ ተጠቃሚ እያደረጋቸው ነው።

ከሰንበት እስከ ሰንበት በሚል የተጀመረው ገበያ ሸማቹን ከአምራቹ ጋር ሳይቆራረጥ እንዲገናኝ በማድረግ የተረጋጋ ግብይት እንዲኖር እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በየአካባቢው የቅዳሜ ገበያ የመጀመሪያ አማራጭ ተደርጎ ይወሰድ እንደነበር አስታውሰው፣ በበአሁኑ ወቅት ሳምንቱ ሙሉ ምርት የሚቀርብበት ገበያ መፈጠሩ የምርት መደበቅና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪን እየተከላከለ መሆኑን ተናግረዋል።

ሸማቹ ከአምራቹ ጋር በቀጥታ መገናኘቱ በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ነዋሪዎች እንደአቅማቸው እንዲሸምቱ እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል።

የወራቤ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ዘኪያ ሽኩሪ በበኩላቸው እንዳሉት በከተማዋ የተቋቋሙ የሰንበት ገበያዎች መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ከአምራቹ ለመሸመት ዕድል ፈጥረዋል።

ሳምንቱን ሙሉ የተጀመረው ገበያ በአቅማቸው የሚፈልጉትን በአቅማቸው ለመግዛት እንዳስቻላቸውና ለብዙዎች እፎይታ መስጠቱን ጠቁመው፣ ገበያው የሸቀጦች ዋጋ እንዲረጋጋ ማድረጉን ተናግረዋል።

እንደ ቲማቲም፣ ሽንኩርትና መሰል አትክልቶች በከፍተኛ ሁኔታ ዋጋቸው ቀንሷል ያሉት ወይዘሮ ዘኪያ፣ ከፋብሪካ ምርቶችም በዳቦ ዱቄት ላይ ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል።

በቡታጅራ ከተማ በዶሮ እርባታ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ንጉሴ ደምበል ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ለንግዱ ማህበረሰብ እንቁላል ሲያከፋፍሉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በሰንበት ገበያ በተመቻቸላቸው የመሸጫ ቦታ የእንቁላል ምርታቸውን ለአካባቢው ማህበረሰብ  በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የሚያስችሉ 100 የሰንበት ገበያዎች እንደተቋቋሙ የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ይሳቅ ማሶሬ ናቸው።

ከሰንበት እስከ ሰንበት ገበያ ያልተቋረጠ የግብይት ሂደት እንዲፈፀም ከማድረግ ባለፈ አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘቱ ውጤት እየታየ መሆኑን ተናግረዋል።

ከእዚህ ጎን ለጎን ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉና ምርት በሚደብቁ ህገወጥ ነጋዴዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር መደረጉን አስታውቀዋል።

በዚህም በ217 የእህል መጋዘኖች ላይ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻም ከ40 ሺህ ኩንታል በላይ የተሸሸገ የጤፍ ተገኝቶ በሰንበት ገበያ ለህብረተሰቡ እንዲቀርብ ተደርጓል ብለዋል።

በቀጣይም በህገወጥ ነጋዴዎች ላይ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የገለጹት 

በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ አቶ ገብረመስቀል ጫላ የተመራ ቡድን በክልሉ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን ሰሞኑን ተዘዋውሮ መመልከቱ ይታወሳል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም