የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ከዓለም ባንክና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከፍተኛ ሃላፊዎች ጋር ተወያየ

151

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10/2016(ኢዜአ)፦ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ያካተተው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ከዓለም ባንክ እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከፍተኛ ሃላፊዎች ጋር ፍሬያማ ውይይት ማካሔዱ ተገለጸ።

በገንዘብ ሚኒሰትሩ አቶ አህመድ ሺዴ የተመራው የልኡካን ቡድን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱን፣ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ አቶ ተክለወልድ አጥናፉን፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር)ን እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ያካተተ ነው።

የልዑካን ቡድኑ ከዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክርስታሊና ጂኦርጄቫ፣ ከአለም ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንትና የምስራቅና የደቡባዊ አፍሪካ ሃላፊ ቪክቶሪያ ክዋክዋ፣ የአለም ባንክ ዓለም አቀፍ ልማት ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አኪህኮ ኒሺዮና ከሌሎች የዓለም ባንክና የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር ተገናኝቷል።


 

በውይይቶችም ላይ ከተነሱት ጉዳዮች መካከል፣ ስለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሁኔታና የወደፊት ተስፋ፣ የተረጋጋ አገራዊ ጥቅል ኢኮኖሚ ለማምጣት እየተሰራ ስላለው የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ ኢኮኖሚያዊ እድገትና የስራ ዕድል ፈጠራ፣ ምርታማነትን ማሳደግ እና የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚን ለማሳለጥ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችይገኙበታል።

ሁለቱም ተቋማት ኢትዮጵያ እየወሰደቻቸው ያሉትን ወሳኝ እርምጃዎች ማለትም ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት እና የዋጋ ንረትን ለመቅረፍ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን እንዲሁም በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ሁለተኛ ምዕራፍ ሀገር አቀፍ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምን አድንቀዋል።

በተጨማሪም አለም ባንክ እና ዓለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምን በሙሉ አቅም ለመተግበር ከማስቻል አኳያ በቀጣይ መደገፍ እና አብሮ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።

 

 

 

 

 



 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም