በአማራ ክልል  የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የመሰረተ ልማት  ግንባታዎች  በመካሄድ ላይ ይገኛሉ

530

ባህር ዳር ፤ ሚያዝያ 10/2016(ኢዜአ)፡-  በአማራ ክልል የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በመካሄድ ላይ እንደሚገኙ  ተገለጸ። 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ያለውን የአስፋልት መንገድ ግንባታ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።


 

በዚህ ወቅት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዱ ሁሴን እንደገለጹት፤ በክልሉ በተደራጀ መንገድ ከሚከናወነው ዘላቂ ሰላም የማስፈን ስራዎች በተጓዳኝ የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ።

ለዚህም በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ከአየር መንገድ እስከ ልደታ ሰፈር እየተገነባ የሚገኘው የአስፋልት መንገድ ግንባታ ማሳያ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የባህር ዳር ከተማን ውበትና ጽዳት የሚመጥኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

በከተማው የተካሄደው ጉብኝትም በልማት ስራዎቹ እንቅስቃሴ የከፍተኛ አመራሩ ድጋፍ የሚያስፈልጉ ጉዳዮችን ለመለየትና አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንደሆነ ገልጸዋል።


 

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምከትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው በከተማ አስተዳደሩ ዛሬ ጉብኝት የተደረገው የአስፋልት መንገድ ግንባታ ጨምሮ 22 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ ስራዎች መሆኑን ገልጸዋል።

የመንገድ ፕሮጀክቶቹ የባህር ዳር ከተማን የመሰረተ ልማት አቅርቦት እጥረት በመፍታት የነዋሪዎችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ እንደሆነም አመልክተዋል።

በተጨማሪም የባህር ዳር ከተማን ውበት አጉልተው የሚያሳዩ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶችን ለማከናወን የጥናት ስራዎች እየተካሄዱ እንደሚገኝ አቶ ጎሹ አስታውቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም