በክልሉ የአካባቢ ብክለትን በመከላከልና በመቆጣጠር  ሂደት ህዝቡ ጠንካራ ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባል..ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

አርባ ምንጭ፤ ሚያዚያ 10/2016(ኢዜአ)፡-  በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአካባቢ ብክለትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው እንቅስቃሴ ህዝቡ ጠንካራ ተሳትፎ እንዲያደርግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ አሳሰቡ።

“ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ” በሚል መሪ ሃሳብ ክልል አቀፍ የብክለት መከላከል ንቅናቄ ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እንደገለጹት፤የአካባቢ ብክለትን መቆጣጠር አለመቻል ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ይዳርጋል።

የሰውና የእንስሳት ህልውናን አደጋ ላይ ከመጣሉም በላይ በቱሪስት ፍሰትና ኢንቨስትመንት ልማት ላይ አሉታዊ  ተጽእኖ እንደሚያስከትል አመልክተዋል ።

በተለይ ኢንዱስትሪዎች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጭ ተቋማት የሚያስከትሉትን የአካባቢ ብክለት ለመከላከል የመፍትሄ ሀሳቦችን የማቅረብ ብሎም ተቋማቱን  መከታተልና  መቆጣጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

በዚህ ረገድ  የክልሉ መንግሥት  አካባቢን ከብክለት ለማዳን መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት  አባቶችና የአገር ሽማግሌዎችን በማሳተፍ እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል።

ህብረተሰቡ በተለይም የፕላስቲክ ቁሳቁሶችን በአግባቡ በመጠቀምና በማስወገድ እንዲሁም የአየር፣ የውሃና የአፈር ሀብቶችን ከብክለት በመጠበቅ ድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ግዛቴ ግጄ በበኩላቸው፤ በአካባቢ ብክለት ሳቢያ በሚመጡ የሙቀት መጠን መጨመር፣ የበሽታ ክስተት፣ በረሃማነት መስፋፋት፣ ምርትና ምርታማነት መቀነስ የህዝብ የመኖር ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን ተናግረዋል ።

"ከተፈጥሮ ጋር ሳንስማማ መኖር አንችልም" ያሉት ሃላፊው፤ ህዝቡ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት አካባቢውን ከብክለት መጠበቅ እንደሚገባ አመልክተዋል።

"ዛሬ በይፋ የተጀመረው ክልል አቀፍ የአካባቢ ብክለት መከላከል ዘመቻ ለስድስት ወራት ይቆያል" ብለዋል።

የአካባቢ ብክለትን በመደበኛ ስራ ብቻ መከላከል የማይቻል መሆኑን ጠቁመው፤  የተለያዩ ተቋማት፣ ህዝብና መንግስት በቅንጅት እንዲሠሩ በማስቻል ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ንቅናቄውን ማሳካት ይገባል ብለዋል።


 

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ያስመዘገበችውን ድል በአካባቢ ብክለት መከላከል መድገም ይገባል  ያሉት ደግሞ የኢፌዴሪ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬነሽ መኩሪያ ናቸው ።

በአሁኑ ወቅት ባለስልጣኑ የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ዜጎች የአካባቢ ብክለትን በመከላከል የፀዳችና የለማች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማውረስ የሚደረገውን ጥረት በተቀናጀ መንገድ መደገፍ እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

ቆሻሻን በአግባቡ መጠቀምና ማስወገድ ባለመቻሉ በሰውና እንስሳት ጤና ላይ ጉዳት ከማስከተልም በላይ ለስርዓተ ምህዳር መዛባትና ለብዝሃ ህይወት የመጥፋት ምክንያት በመሆኑ መከላከል ይገባናል ብለዋል።

የፕላስቲክ ምርቶች ሳይበሰብሱ ለብዙ ዘመናት የሚቆዩ በመሆናቸው ህብረተሰቡ ከፕላስቲክ ምርት ይልቅ ባህላዊና አገር በቀል ቁሳቁሶችን መጠቀም እንደሚገባውም ወይዘሮ ፍሬነሽ ተናግረዋል።

በንቅናቄ መድረኩ በክልሉ የሚገኙ 10 ዞኖች  በቀጣይ ተራራን እንዲያለሙ የተራራ ልማት ካርታ ርክክብ ተደርጓል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም