በክልሉ ለትምህርት ዘርፍ በተገኘ ከ530 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸው ተገለጸ

345

ቦንጋ ፤ ሚያዚያ 10 / 2016 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለትምህርት ዘርፍ ከህብረተሰቡና ከባለሀብቶች  በተገኘ ከ530 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ  የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።

በዘርፉ ከተከናወኑት መካከል አዲስ ትምህርት ቤቶችና የተጨማሪ መማሪያ ክፍሎች ግንባታ እንዲሁም የመማሪያ መጽሐፍት በማሳተም ለተማሪዎች ተደራሽ ማድረግ እንደሚገኙበት ቢሮው አመልክቷል። 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አልማው ዘውዴ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ፤ በበጀት ዓመቱ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን በተደረገው ርብርብ ውጤታማ ስራዎች ማከናወን ተችሏል።

በዘመኑ ለትምህርት ዘርፍ ሀብት ለማሰባሰብ በተደረገው ጥረት ከህብረተሰቡና ከባለሀብቶች ከ530 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መገኘቱን ገልጸዋል።

በተገኘው ድጋፍ በየደረጃው የትምህርት ቤቶች ደረጃ ለማሻሻልና የተማሪ የመማሪያ መጽሐፍት ሕትመት ስራ ትኩረት ተሰጥቶት  ሲከናወን መቆየቱን አስረድተዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከተከናወኑ ዋና ዋና ስራዎች መካከል 14 አዲስ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ 31 ቤት መጽሐፍት፣ 1 ሺህ 555 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታና ጥገና እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

እንዲሁም በገጠር ቀበሌዎች የመምህራን መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እና ሌሎችም  መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ተግባራት መከናወናቸውን አመላክተዋል።

በቅድመ መደበኛና በአንድኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመማሪያ መጽሐፍትን ለተማሪዎች ተደራሽ ከማድረግ አንፃርም በየዞኑ ጭምር ህበረተሰቡን በማሳተፍ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ የኮንታ ዞን  64 ሺህ 277  መጽሐፍትን በማሳተም ለተማሪዎች ተደራሽ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

የቀሩት ዞኖች  ባሰበሰቡት ከ116 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 614 ሺህ የሚጠጋ መፅሐፍት ህትመት እየተከናወኑ እንደሚገኙ የቢሮው ሀላፊ አውስተዋል።

በክልሉ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻልም በተቀናጀ አግባብ  ለተማሪዎች አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ  አቶ አልማው ተናግረዋል።

በተለይ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ 24 ሺህ 499 ተማሪዎችን በመመዝገብ የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን አብራርተዋል።

እንደ አቶ አልማው ገለፃ በቀጣይም ለተማሪዎች ምገባ፣አዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ የመምህራን አቅም ማጎልበት እና በትምህርት ቤቶች ጠንካራ የአሰራር ስርዓትን ለመዘርጋት ትኩረት ተሰጥቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም