በአፋር ክልል ዱብቲ ወረዳ  በ138 ሄክታር መሬት ላይ  አትክልትና ፍራፍሬ  በመስኖ እየለማ  ነው

196

ሰመራ፤ ሚያዚያ 10/2016(ኢዜአ)፡- በአፋር ክልል ዱብቲ ወረዳ   በ138 ሄክታር መሬት ላይ የተለያየ አትክልትና ፍራፍሬ እየለማ እንደሚገኝ ተገለጸ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ  አወል አርባ በዱብቲ ወረዳ  ጉሩሞዳሊና ገይዴሪ ቀበሌዎች በመስኖ እየተካሄደ ያለው የልማት እንቅስቃሴ በመስክ ተዘዋውረው ተመልክተዋል። 

በዚህ ወቅት የዱብቲ ወረዳ የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መሐመድ ኖራ  እንደገለጹት፤ በወረዳው በ138 ሄክታር መሬት ላይ  የተለያየ አትክልትና ፍራፍሬ በመስኖ እየለማ ይገኛል። 

ከልማቱ ውስጥ ሽንኩርት ፣ ቲማቲም፣  ሙዝና ሐብሐብ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ርዕስ መስተዳደሩ በበኩላቸው፤  ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እንደ አገር ብሎም እንደ ክልል ገበያው ላይ እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ አለመረጋጋት ለማስቀረት የመስኖ  ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል። 

ለዚህም በዱብቲ ወረዳ  በመስኖ እየለማ ያለውን አትክልትና ፍራፍሬ የጠቀሱት ርዕሰ መሰተዳድሩ፤ ያለማና ለአረም ተጋልጦ የነበረውን መሬት  ለልማት እንዲውል መደረጉ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

በመስኖ የማልማቱ ተግባር እየተጠናከረ መምጣቱን አመልክተው፤ በልማቱ ለተሰማሩ ከፊል አርብቶ አደሮች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

በአፋር ክልል ደረጃ የአዋሽ ወንዝን  በመከተል በመስኖ የተለያየ የአዝርዕት ሰብልና  ፍራፍሬ በሰፋት እየለማ እንደሚገኝ ተወስቷል።

በመስክ ምልከታው  የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና የወረዳ አመራር አባላት ተሳትፈዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም