ባለስልጣኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ10 ሚሊዮን  ሜትሪክ ቶን በላይ ጭነት ማጓጓዙን አስታወቀ

124

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 10/2016(ኢዜአ)፦  ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ10 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ጭነት ወደ አገር ውስጥ ማጓጓዙን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አብዱልበር ሸምሱ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በ2016 በጀት አመት ዘጠኝ ወራት በገቢ ጭነትና ሌሎች ዘርፎች የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ዘርዝረዋል።

ባለስልጣኑ በበጀት አመቱ ነዳጅ ፣ ማዳበሪያና የኮንቴነር እቃዎችን ጨምሮ ከ14 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ጭነት ወደ አገር ውስጥ ለማጓጓዝ እቅድ ይዞ ወደ ስራ መግባቱን አስታውሰዋል።

በዚህም ተቋሙ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከአስር ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ጭነት ማጓጓዙን ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ የሎጅስቲክ አገልግሎቱን ለማዘመን የሚረዳውን የአሰራር ስርአት ከወደብ ጀምሮ የመዘርጋትና የግል ባለሃብቶችን በሎጀስቲክ ዘርፍ በማሳተፍ አገልግሎቱን ለማሳለጥ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህን ተከትሎ በተያዘው በጀት አመት የግሉ ዘርፍ በመልቲሞዳል ትራንስፖርት ዘርፍ እንዲሳተፍ መፈቀዱን ተከትሎ ብቁ መሆናቸው ለተረጋገጠ ሶስት ድርጅቶች እውቅና መሰጠቱን አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ የመልቲሞዳል ሽፋን 60 በመቶ መድረሱን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ በቀጣይ ምጣኔውን የበለጠ ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የአገር ውስጥ ጭነት 85 በመቶ የሚወጣበትና የሚራገፍበትን የሞጆ ደረቅ ወደብ የማስፋፊያ ስራ በፍጥነት በማጠናቀቅ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሳለጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በማሪታይም ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ ሙያተኞችን ለማሰልጠን ከተለያዩ አገራት ጋር በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

 

 

 

 

 

 


 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም